በህዝብና በመንግስት ጥረት ክልሉ መረጋጋትና ሠላም መስፈን ችሏል-አቶ ርስቱ ይርዳው

57

ሐዋሳ (ኢዜአ) ነሐሴ 3/2012  በደቡብ ክልል ህዝብና መንግስት በጋራ በመስራታቸው በአብዛኛው አካባቢ ሲከሰቱ የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ተፈትተው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለፀ ፡፡

አቶ ርስቱ ይህን የተናገሩት እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው፡፡

በየአከባቢው እየተነሱ የነበሩ የመዋቅር ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ ተቆርቋሪ መስለው እኔ አስመልስልሃለሁ በሚል እሳቤ በህዝቡ ውስጥ የተሰገሰጉ ግለሰቦችና አመራሮች ለክልሉ የጸጥታ መደፍረስ ዋነኛ መንስኤ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በክልሉ ሙሉ በሙሉ በሚቻል ሁኔታ ሠላም መስፈኑ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው አካባቢው የትርምስ ቀጠና ከመሆን ተርፎ ዛሬ ስለ ልማት መመካከር እንደተቻለ አስረድተዋል ።

የተፈጠረው መልካም አጋጣሚና ስኬት በህዝቡ ሠላም ፈላጊነት የተገኘ በመሆኑ ዕውቅናና ክብር ይገባዋል ብለዋል፡፡

በሃገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ነውጠኞች ደቡብ ክልልን ትኩረት አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ ያመለከቱት አቶ ርስቱ ይህ እየከሸፈ ቢመጣም አሁንም አድብተው እየጠበቁ ስለመሆናቸው ምልክቶች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ሰላምን የሚያደፈርሱና የልማትና የብልጽግና ጉዞው ለማደናቀፍ የሚሠሩ ሃይሎችን ለማጥራት እንደሚሠራም አስረድተዋል ።

የክልሉ ምክር ቤት አባላትም ይህንኑ ጥረት  ማገዝ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ህዝብ ጥያቄ የሚያነሳው የሚሰማና ለዕድገትና ለለውጥ የሚሰራ መንግስትና ፓርቲ በመፈጠሩ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥያቄውን በማጣመም ህዝብንና መንግስትን ለማለያየት የሚደረገውን ሙከራ እያስወገድን ወደ ፊት እንጓዛለን ብለዋል፡፡

አፍራሽ ሀይሎች ያገኙትን አማራጭ ሁሉ ተጠቅመው የክልሉን ሠላም በማደፍረስ የለውጡን ሂደት ለመቀልበስ በብሄር ማንነትና በሃይማኖት ሽፋን እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ሃላፊና የምክር ቤቱ አባል አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸው፡፡

ለዚህ ደግሞ የአደረጃጀት ጥያቄ መነሻ እንደሚያደርጉ ገልጸው የምክር ቤቱ አባላት ይህ ጥያቄ አግባብ ቢሆንም አካሄዱ ህዝብን በሚጠቅም መልኩ እንዲሆን ማድረግ ይገባናል ብለዋል፡፡

ካገኘነው ሠላም በመነሳት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እስከ ታች ያሉ የመንግስት መዋቅሮችና የህዝብ አደረጃጀቶች በመጠቀም በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ክልሉ እንዳይረጋጋና በውስጡ ያሉ ጸጋዎችን ተጠቅሞ ወደተፈለገው ልማትና ብልጽግና ለመገስገስ የህግ የበላይነት ያለመከበር ማነቆ መሆኑን ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ይሁን አሰፋ ተናግረዋል።

የፍትህ ተቋማትና ፍርድ ቤቶች ደካማ በመሆናቸው የክልሉ መንግስት የማስተካከያ አማራጭ መውሰድ እንደሚገባው አቶ ይሁን ጠቁመዋል ።

ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ከድጃ አንደታ በበኩላቸው ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሸረሪት ድር የተያያዘና የተሳሰረ ነው ብለዋል፡፡

በመስቃንና ማረቆ ማህበረሰብ መካከል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ዜጎች መንግስት መመልከትና የህግ የበላይነትን በማስከበር ወደቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ህዝቡን ለዚህ ችግር የዳረጉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል ።

የክልሉ ምክር ቤት እያካሄደ ባለው ጉባኤ በበጀት ዓመቱ የክልሉ መንግስት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ተሰጥተውበት በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም