በምሥራቅ ወለጋ ዞን ከዕቅድ በላይ ገቢ ተሰበሰበ

66

ነቀምቴ ኢዜአ ነሐሴ 03/2012. የምሥራቅ ወለጋ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ፅህፈት ቤት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 468 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ ከእቅዱ በላይ ማሳካቱን ገለፀ ። 

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ዲቢሣ እንደገለፁት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች ከመደበኛና ማዘጋጃ ቤት ገቢ 434 ነጥብ 6 ሚሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር ።

የተቀናጀ ስራ በማከናወን በዓመቱ 468 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ እንደተቻለ ገልፀው ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል ።

ከዓመታዊ አቅዱንም ሆነ ከቀዳሚው ዓመት ብልጫ ያለው ገቢ መሰብሰብ የተቻለው የባለሥልጣኑ ሠራተኞች፣ የየዘርፉ መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ፣ የዞን አስተዳደርና የድርጅት ጽህፈት ቤቶች በኃላፊነት መንፈስ ተቀናጅተው መስራት በመቻላቸው ነው ብለዋል ።

በተለይ ደግሞ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሳይበግረው ግዴታውን በጊዜው በመወጣቱ ለገቢው ማደግ ገንቢ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አቶ መኮንን ተናግረዋል ።

ከዞኑ ግብር ከፋዮች መካከል በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ የተሰማሩት አቶ አህመድ መሐመድ በሰጡት አስተያየት ግብር በጊዜ መክፍል ከግዴታም በላይ ጥቅሙ ለራስ በመሆኑ የሚጠበቅብንን በጊዜው ከፍለናል ብለዋል ።

በምግብ ቤት ንግድ የተሰማሩት አቶ አዲሱ ተሰማ በበኩላቸው  ከሕዝቡ የሚሰበሰበው ገቢ ተመልሶ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማሟላት ስለሚውል በወቅቱ የሚፈለግብኝን ግብር ከፍያለሁ ሲሉ ተናግረዋል ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሥመራ ኢጃራ የዞኑ ግብር ከፋይ ሕብረተሰብ የሚፈለግበትን ገቢ በወቅቱ ከፍሎ ለማጠናቀቅ ያሣየው ተነሳሽነትና አስፈፃሚ አካላት ላደረጉት ርብርብ ምስጋና አቅርበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም