ችግኝ በመንከባከብ ለማሳደግ እንደሚጥሩ በሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ

50

ፍቼ  ነሐሴ 02/2ዐ12 (ኢዜአ)  የአካባቢያቸውን የደን ሽፋን እንዲጨምር የተከሉትን ችግኝ በመንከባከብ ለማሳደግ እንደሚጥሩ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ከ165 ሚሊዮን የሚልቅ ችግኝ  መትከላቸው ተመልክቷል።

ከነዋሪዎቹ መካከል በግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ ዛሬ በተካሄደው የችግኝ መረሃ ግብር የተሳተፉት  የሰሜን ሸዋ ዞን አባ ገዳ ዘነበ ቱፋ የቆየውን የአካባቢያቸውን ልምላሜና ምርታማነት ለመመለስ ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ለመወጣት በስራው መካፈላቸውን ተናግረዋል።

ይኸም ከቆየው የኦሮሞ ደንና እፅዋትን የመንከባከብ ባህል ጋር የሚያያዝ በመሆኑ መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የዞኑ የደን ባለሙያ አቶ ስመኝ ደበሌ በበኩላቸው በየአካባቢው የተካሄደው የችግኝ ተከላ በእንክብካቤና ድጋፍ ከታገዘ የአካባቢውን የደን ሽፋን ከማሳደግ አልፎ የህብረተሰቡን ኑሮ ይለውጣል ብለዋል፡፡

በተለይም በአርሶ አደሩ ማሳ አካባቢ የሚተከል የፍራፍሬ፣ መኖና ማገዶ ችግኝ ጠቀሜታ የላቀ በመሆኑ የተተከለውን በመንከባከብ ለማሳደግ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የሰላሌ ዩኒቨርስቲ መምህርት ወይዘሮ ዘሐራ አህመድ በሰጡት አስተያየት በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻር መርሃ ግብር ከሃምሳ የሚበልጥ ችግኝ  በስራ አካባቢያቸው ቀድመው መትከላቸውን አስታውሰው የተከሉትንም በዘላቂነት እንደሚንከባከቡ ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከልም ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ብርሃኑ ናቸው።

የተከለው ችግኝ እንዲፀድቅ በቀጣይ እቅድ ወጥቶ ክብካቤና ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤተ ምክትል ኃላፊ አቶ ሂርጳሳ አዱኛ  በዞኑ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  160   ሚሊዮን ሀገር በቀል ችግኝ ለመትከል ከታቀደው በላይ  በተራቆቱ አካባቢዎች መከናወኑን አስታውቀዋል።

በአምናው የክረምት ወቅትም ከተተከለው 145 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ ባለፈው ሚያዝያ በተካሄደው የመጨረሻ የችግኝ ብቅለት ማረጋገጫ ጥናት ከሰማንያ አምስት በመቶ በላይ መጽደቁን አስረድተዋል።

ዘንድሮም የእንክብካቤ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በተገባደደው የሐምሌ ወር በተከናወነው የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር 325ሺህ  አርሶ አደሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የከተማ ነዋሪዎች ፣ የሀገር መከላከያና ፖሊስ አባላት በነፍስ ወከፍ እስከ ሃምሳ ችግኝ በ17ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በመትከል መሳተፋቸውን አቶ ሂርጳሳ  ገልጸዋል፡፡

በክረምቱ የተተከለው ችግኝ ሲጸድቅ ከሶስት ዓመት በኋላ የዞኑ የደን ሽፋን አሁን ካለበት 26 በመቶ ወደ 31 በመቶ እንደሚያሳድገውም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም