የአየር ፀባይ ለውጥ ወደ ከተማ የሚገፋቸው ሚሊዮን ነፍሶች

280

የአየር ፀባይ ለውጥ ወደ ከተማ የሚገፋቸው ሚሊዮን ነፍሶች

የአየር ንብረት ቀውስ ሰዎች "ገጠር ለምኔ" ብለው ወደ ከተማ እንዲሰደዱ ከሚገፉ ቀዳሚ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን የአለም ባንክ ሪፖርት ያሳያል።

ከዚህ ባለፈ የአየር ንብረት ቀውስ የጤና ቀውስ ነው ይላሉ ምሁራኖች።

የምድር ሙቀት መጨመር እንዲከሰት የሚያደርጉት ተመሳሳይ ልቀቶች የምንተነፍሰውን አየር ለመበከል ፣ የልብ በሽታ፣ የደም ቧንቧ፣ የሳንባ ካንሰር እና ኢንፌክሽኖች እንዲገጥሙንም በማድረግ አቻ የላቸውም፡፡

“የአየር ብክለት አዲሱ ትንባሆ ነው፣ መንስኤውም በብዙ ሲጋራዎች የሚሞቱ ጎልማሶችን ይወክላል፤ ከሁሉም በላይ ሕፃናት፣ አዛውንቶች፣ እርጉዝ ሴቶችና አዋቂዎችን፣ የበሽታ መከላከያ ስርዓታቸው የተዳከመ ጎልማሶችን ያጠቃል” በማለት የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር፣ የሕዝብ ጤና ፣ የአካባቢ እና ማህበራዊ ውሳኔዎች ዳይሬክተር ዶክተር ማሪያ ኔራ ይናገራሉ።

የአየር ፀባይ ለውጥ በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ሳይሆን ህዝቦችን ወደ ከተማ እንዲሰደዱ የሚያደርግበትን መንገድም እንመለከታለን።

በአየር ፀባይ ለውጥ ቀውስ የሚከሰት የጎርፍ አደጋ፣ ድርቅ፣ የምግብ ዋስትና መጓደል ሰዎች ወደ ከተማ እንዲሰደዱ ይገፏቸዋል።

የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲን ዳሰሳ መሰረት በማድረግ ባወጣው ምልከታ እኤአ በ2037 በኢትዮጵያ በከተሞች የሚኖረው ህዝብ ቁጥር 42 ነጥብ 3 ሚሊዮን ይጠጋል በማለት ግምቱን አስቀምጧል።

በኢትዮጵያ የሚታየው ፈጣን ከተሜነት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በከተሞች ያለውን የጉልበት ሰራተኛ በሁለት እጥፍ ያሳደገ ሲሆን ምጣኔው እኤአ በ2030 ወደ 82 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ሪፖርቱ ያሳያል።

በቅርቡ ፕሮፓብሊካ የተባለ ቡድንና ኒውዮርክ ታይምስ መፅሄት በጋራ ባደረጉት ጥናት ገደቡን ያለፈ የከተሜነት መስፋፋት አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያስከትል ጠቁመዋል።

በጥናት ግኝታቸው” በህዝብ በተጨናነቁ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች ደረጃቸውን ባልጠበቁና መሰረተ ልማት ባልተሟላባቸው መንደሮች ለመኖር ስለሚገደዱ ፅንፈኝነትንና ብጥብጥብን እንዲመርጡ ይገደዳሉ ይላሉ።

በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥር ተከትሎ አዲስ አበባና መሰል ከተሞች የከተሜነት መስፋፋት እየታየባቸው መሆኑን ዘ ኢንሳይደር የተባለው ድረ ገፅ ዘግቧል።

ለዚህ ደግሞ የአየር ፀባይ ቀውስ ሚሊዮኖች የመኖሪያ ቀያቸውን በመልቀቅ ወደ ከተማ እንዲሰደደዱ እያደረጋቸው ነው። ከዚህ በባሰ ድንበር አቋርጠው ለከፋ ስደትም ዳርጓቸዋል።

የኢኮኖሚ አንትሮፖሎጂስት የሆኑት ጃሰን ሀይከል ለኢንሳይደር በኢሜል በሰጡት አስተያየት “በአየር ፀባይ ለውጥ የሚከሰት የጎርፍና የድርቅ አደጋ በአለም ላይ የሚገኙ አንዳንድ የገጠር ከተሞችን ነዋሪ አልባ አድርገዋል ። ”

ይህ ሁኔታ ደግሞ ሰዎች የመኖሪያ ቀያቸውን በመልቀቅ የጉልበት ስራ ፍለጋ ወደ ከተማ እንዲሰደደዱ ያደርጋቸዋል ይላሉ ምሁሩ።

በኢትዮጵያ እኤአ በ2028 በከተሞች የሚኖረው ህዝብ ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥር 30 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው የአለም ባንክ ትንበያ ያመለክታል።

ፈጣን የከተማ እድገት ደግሞ ሰዎች ደረጃቸውን ባልጠበቁ መኖሪያ ቦታዎች እንዲሰበሰቡ ያስገድዳቸዋል ብሏል። 

በአለም ላይ የከተሞች መስፋፋት ከሚከናወንባቸው ቦታዎች መካከል 40 በመቶ የሚጠጉት ደረጃቸውን ያልጠበቁ መንደሮች መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እኤአ በ2017 ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።

የዚህ አንዱ ማሳያ ደግሞ በከተማችን በመከናወን ላይ የሚገኘው የመልሶ ማልማት ስራ ነው።

ጃሰን ሀይከል እንደሚሉት የተጨናነቁ መንደሮች መስፋፋት “የድህነት ምንጭ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የማህበራዊ ቀውስ" መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ።

ፈጣን የከተማ መስፋፋት የስራ እድል ፍላጎቱን በእጅጉ ስለሚያሳድገው ይህንን ፍላጎት በራሱ መሙላት ፈታኝ ነው።

በዓለም ባንክ ሪፖርት መሰረት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በኢትዮጵያ ያለው የጉልበት ሰራተኞች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል።

በመሆኑም አሁን ላይ በከተሞች የሚታየውን ስራ አጥነት ለመቅረፍ እኤአ ከ2019 እስከ 2035 ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ በየአመቱ 1 ሚሊዮን የከተማ የስራ እድል መፍጠር ይጠበቅባታል ብሏል።

“በኢትዮጵያ የታየው ሁኔታ አለም ወደ ፊት አስከፊ ነገር ሊገጥማት እንደሚችል ማሳያ ነው። የአለም የሙቀት መጠንን ለመቀነስ ስር ነቀል ተግባር ማከናወን ካልተቻለ ችግሩ ከመባባስ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም “ይላሉ ጃሰን ሀይከል።

ፕሮፓብሊክና ኒውዮርክ መጋዚን የሰሩት ጥናት ጉድለት ቢኖርበትም የደረሱበት መደምደሚያ እንደሚያሳየው ”የአየር ፀባይ ቀውስ አሁን ላይ ለሚታዩት አለመረጋጋቶች፣ የብጥበጥ መነሻዎች እና ለበርካታ ሰዎች መሰደድ" ዋና ምክንያት መሆኑን ነው።

በህይወት የሌሉት የቀድሞው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ምሁር ኖርማን ማየርስ እኤአ በ2050 በአየር ፀባይ ቀውስ የተነሳ 200 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ከመኖሪያ ቀዬው ይሰደዳል በማለት ግምታቸውን አስፍረው ነበር።

ጃሰን ሀይከል እንደሚሉት” በአየር ፀባይ ቀውስ ክፉኛ ከተጎዱት አገራት መካከል አብዛኛዎቹ ለቀውሱ ምንም አይነት አስተዋጽኦ የማያበረክቱ ናቸው።

"ሁሉም ሰው ደህንነቱ የተጠበቀና ለኑሮ ምቹ የሆነ ፕላኔት እንዲኖረው ማረጋገጥ ግድ ይላል፤ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትግልም በዚህ ዙሪያ ማነጣጠር አለበት" ብለዋል።

ለአለም የአየር ፀባይ ቀውስ 68 በመቶ አስተዋጽኦ ያላቸው አስር አገራት ሲሆኑ ቻይና 26 በመቶ፣ አሜሪካ 13 በመቶ አውሮፓ ህብረት 7 ነጥብ 8 በመቶ ድርሻ አላቸው።

እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞችና ነዋሪዎች ደህንነቱ የተረጋገጠና ቀጣይነት ያለው ህይወት እንዲኖራቸው የቀውሱ መነሻ አገራት ለአየር ፀባይ ቀውስና ለስደተኞች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለባቸው።

አሜሪካና ሌሎች ያደጉ አገራት” ስደተኞችን በፈቃደኝነት ለመቀበል ካልሆነ ደግሞ በመኖሪያ ቀያቸው እያሉ ለመደገፍ ወደ ኋላ ካሉ የሚደርሰው ጉዳት ሊቀለበስ የማይችል መሆኑን” ፕሮፓብሊካና ኒውዮርክ ታይምስ በጋራ ያደረጉት ጥናት ይጠቁማል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አዴሲና አኪንዉሚ እኤአ በ2019 እንደተናገሩት “አፍሪካ የአየር ፀባይ ለወጥ ቀውሱን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት የምትጠይቀው የገንዘብ ድጋፍ ልመና ሳይሆን ፍትሃዊ የአየር ፀባይ ውሳኔን መጠየቅ ነው።” 

“አሁን ላይ እየተደረገ ያለው የእርዳታ አሰጣጥ ተግባር ትርጉም ያለው መፍትሄ አያስገኝም። የበለጸጉ አገራት ለቀውሱ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ የድንጋይ ከሰልን መጠቀም በማቆም ለተጎዱ አገራት ካሳ መክፈል አለባቸው” በማለት ጃሰን ሀይከል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ላለው ተፅዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ በመሆኗ ጊዜ እየቆጠረ የሚከሰተው ድርቅ የሚያሳድረውን ጫናም ሆነ የአየር ንብረት ለውጡን የሚቋቋም አቅም በማጣቷ ልጆቿ ወደ ከተማ አለፍ ሲሉም ወደ ባህር ማዶ እየተሰደዱ ነው።

የደን ሀብትን ማብዛት የአየር ንብረት ለውጥ እያሳደረ ያለውን ተዕፅኖ ለመቋቋም ዓይነተኛ መፍትሔ መሆኑ እርግጥ ነው።

በኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሳታፊ በመሆን አሻራችንን ማሳረፍና ለችግኞቹ ፅድቀትና እድገት እንክብካቤ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም