ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ከተፈጥሮ ጋር ሰላም ለመፍጠር የተጀመረው ሥራ መጠናከር አለበት..ሚኒስትር ሙፈሪያት

79

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 2/2012 ( ኢዜአ)ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ከተፈጥሮ ጋር ሰላም ለመፍጠር የተጀመረው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አሳሰቡ።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የችግኝ ተከላ ለተፈጥሮ አደጋ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ቀድሞ ለመከላከል ያስችላል ብሏል።

የሰላም ሚኒስቴርና በሥሩ ያሉ ተቋማት 300 የሚደርሱ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በጋራ ዛሬ ችግኝ ተክለዋል።

ሚኒስትሯ  በዚሁ ወቅት እንዳስገነዘቡት ችግኝ መትከልና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ሰላምን የሚያረጋግጥባቸው መንገዶች አንዱ በመሆኑ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።

ሚኒስቴሩ ከዚህ በፊት የተከላቸው ችግኞች 80 በመቶ መፅደቃቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ሙፈሪያት፤ ዘንድሮ እየተተከሉ ያሉትን ችግኞች በተቋማቱ ሰራተኞችና በአካባቢው ማህበረሰብ ለመንከባከብ እንዲቻል ምቹ ሁኔታን ፈጥረናል ብለዋል።

በተለይ በሕዝብ ተሳትፎ ላለፉት ሁለት ዓመታት የተካሄዱት የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ተግባራት ባህል ሆነው መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ምክንያት በሚደርስ ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋ መቀነስ የሚቻለው የችግኝ ተከላ ተጠናክሮ ሲቀጥል ነው ያሉት ደግሞ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመነ ዳሮታ ናቸው።

ችግኝ በመትከል ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጥቅም በተጨማሪ የተፈጥሮ አደጋ ከደረሰ በኋላ የሰው ሕይወትንና ሃብትን የማዳን ሥራ ቀድሞ ወደ መከላከል ለመቀየር እንደሚያስችል አብራርተዋል።

በመሆኑም ዜጎች  አረንጓዴ ዐሻራን ማሳረፍ ባህል ሆኖ እንዲቀጥሉ ምክትል ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ጌቱ ተክለዮሃንስ በበኩላቸው ሰራዊቱ ከተሰማራበት የሰላም ማስከበር  ተግባር  በተጓዳኝ ችግኞችን በመትከል፣በመንከባከብና አካባቢን በማልማት ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በተያዘው የክረምት ወቅት አምስት ቢሊዮን ችግኞች በመተከል ላይ ናቸው። ችግኞቹ በዋነኝነት የተፈጥሮ ሚዛንን የሚጠብቁና ለምግብነት ይውላሉ።

ባለፈው ዓመት ከተተከሉት አራት ቢሊዮን ችግኞች 80 ከመቶ ያህሉ መጽደቃቸውን የግብርና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም