የኮሮና ለመከላከል የተጀመረው ዘመቻ ስኬታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

51

ባህርዳር ነሐሴ 1/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የተጀመረው ዘመቻ ስኬታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ ተጠየቀ። 

የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህክምና ላብራቶሪ ዳይሬክተር አቶ ማንአምኖት ተገኝ እንደገለጹት ለሁለት ሳምንት የሚቆየው የኮሮና ምርመራ ዘመቻ ዛሬ ተጀምሯል።

በዘመቻውም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚከናወን አመልክተው በዚህም 42 ሺህ የምርመራ ናሙናዎችን ለመውሰድ ታቅዶ ወደስራ መገባቱን አስታውቀዋል።

ምርመራው ትኩረት አድርጎ የሚከናወነው በሆስፒታሎች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎችና ሌሎች ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው ብለዋል።

ምርመራውም በክልሉ ቀደም ሲል ተከፍተው አገልግሎት ይሰጡ በነበሩ ስምንት የምርመራ ላብራቶሪዎች እንደሆነ ጠቁመው በደብረማርቆስና መተማ ከተሞች ተጨማሪ 2 ላብራቶሪዎችን ስራ እንደሚጀምሩ  አስረድተዋል።

የመመርመሪያ ኪቶችና ሌሎች ግብዓቶች ተሟልተው የቀረቡ በመሆኑ በዘመቻው በየቀኑ 3ሺህ በላይ ናሙናዎችን በመውሰድ ዕቅዱን ለማሳካት በትኩረት እንደመሰራ ገልጸዋል።

ምርመራውን በሶስት ፈረቃ  የሚያከናውኑ የላብራቶሪ ባለሙያዎች በየማዕከላቱ መመደባቸውን አመልክተዋል።

ለሁለት ሳምንት የሚካሄደው ዘመቻ ውጤትም ወረርሽኙ ያለበትን ደረጃ በማመላከት መንግስት በቀጣይ የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትን ለመክፈትና ላለመክፈት አቅጣጫ ጠቋሚ መረጃ ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል ብለዋል።

በዘመቻውም ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ያላነሱ ቤቶች እንደሚገበኙ ጠቁመው  ህብረተሰቡም ለሚወሰዱ ናሙናዎች ተባባሪ በመሆን የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት አጋዥ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

ለዘመቻ ስኬታማነት  ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉም  ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል። 

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሐምሌ 30/2012 ዓ.ም ድረስ 34 ሺህ ናሙናዎች ተወስደው ምርመራ መደረጉም ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም