ቢሮው ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርግ ነው

65

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 01/2012 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለ18 የክልሉ ከተሞች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ቢሮው ይህን ያስታወቀው በኮቪድ-19 ምክንያት በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ለሚገኙ ችግረኛ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

በእዚህም ስንዴ፣ ዱቄት፣ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክቷል።

ድጋፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ በከተሞቹ የሚኖሩ አቅመ ደካማና ችግረኛ ወገኖችን ለማገዝ ታስቦ የሚደረግ መሆኑም ነው የተገለጸው።

በመግለጫው እንዳስታወቁት ቢሮው ድጋፉን ያደረገው ከሌሎች የክልሉ ስምንት ቢሮዎች ጋር በመሆን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው።

የኦሮሚያ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል ከድር እንዳሉት ወረርሽኙ በህብረተሰቡ ላይ እያስከተለ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማቃለል ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ይደረጋል፡፡

ከፌደራል መንግስት በተገኘ ድጋፍ ለ38 ከተሞች ለእያንዳንዳቸው አምስት የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ከተሞቹ ለሚሰጡት ማህበራዊ አገልግሎቶች ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የተፈጠረባቸውን ጫና ለማቃለል ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል፡፡

እንደኃላፊው ገለጻ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፉ በክልሉ ለሚገኙ 18 ከተሞች የሚውል ነው።

ኑሮ ከእጅ ወደአፍ ለሆነባቸው ችግረኛና አቅመ ደካማ ወገኖች ድጋፉ የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በ18ቱ ከተሞች በእያንዳንዳቸው ከ700 በላይ የሚሆኑ አባውራና እማውራዎች ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን በአጠቃላይ ከ13 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖች የድጋፉ አካል እንደሚሆኑ ነው የቢሮ ኃላፊው የገለጹት፡፡

"ቢሮው ከተለያዩ የክልሉ ቢሮዎች ጋር በመተባበር ባለሃብቶችንና አጋዥ አካላትን በማስተባበር በሌሎች የክልሉ ከተሞችም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሰው መግለጫው፣ አሁን የሚደረገው ድጋፍ ከዚህ ቀደም ድጋፍ ባልተደረገባቸው ከተሞች መሆኑን አስረድቷል፡፡

የኮሮናቫይረስ መስፋፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉም ዜጋ ሳይዘናጋ ራሱንና ቤተሰቡን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም