በእነ አዲሱ ቶሎሳ እና እነ አራፋት አቡበከር ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ 12 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ

54

አዲስ አበባ  ነሐሴ 01/2012(ኢዜአ) በወንጀል ድርጊት በተጠረጠሩት በእነ አዲሱ ቶሎሳ እና እነ አራፋት አቡበከር ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ 12 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ።

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው ቀርቦ ታይቷል።

በእነ አዲሱ ቶሎሳ መዝገብ አምስት ተጠርጣሪዎች የቀረቡ ሲሆን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በተጠርጣሪዎች ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ ውጤት በዝርዝር አቅርቧል።

ባለፉት ቀናት አከናወንኩ ያላቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርቧል።

መርማሪ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት በተፈጠረው ሁከት በትራንስፖርት ዘርፍ ግምቱ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ጉዳት መድረሱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ማሰባሰቡን ገልጿል።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን በኃይል እንዲመለስ ማድረግ፣ በቡራዩ ከተማ የሰው ህይወት መጥፋትን ጨምሮ ጉዳት መድረስ፣ ''በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት መጣል አለብን'' በማለት ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ማሰባሰቡን ገልጿል።

እንዲሁም የምስክሮች ቃል መስማቱን ለችሎቱ አስረድቷል።

ፖሊስ በእነ አራፋት አቡበከር መዝገብ ስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ ባደረገው ምርመራ ተመሳሳይ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን ገልጾ፤ ግለሰቦቹ በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩና መዝገባቸው ለፍርድ ቤቱ እንዲመች ተደርጎ መቅረቡን አስረድቷል።

በእነ አራፋት መዝገብ ውስጥ ሰባተኛ ተጠርጣሪ ቦና ትብሌ ላይ ምርመራ በማለቁ በሌላ መዝገብ የቀዳሚ ምርመራ ሂደት ውስጥ በመኖሩ በዛሬው ችሎ አልቀረበም።

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኞቻቸው ላይ የቀረበው ማስረጃ በሌሎች መዝገቦች የቀረቡ ጉዳዮች በመሆናቸው ፍርድ ቤቱ መዝገቦቹን አገናዝቦ እንዲያይላቸው ጠይቀዋል።

ደንበኞቻቸው የተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና የሚያስከለክል አለመሆኑ፣ ለምርመራ በቂ ጊዜ መሰጠቱንና ተጠርጣሪዎቹ ለአገር ልማት ወሳኝ የሆኑ ወጣቶች መሆናቸውን በመግለጽ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሳይሰጥ የዋስ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው በመጠየቅ አቤቱታ አቅርበዋል።

ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው የቤተሰብ ችግር እንዳጋጠማቸውና ቤተሰብ እየጠየቃቸው እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በኮሮናቫይረስ ተይዞ የነበረው ተጠርጣሪ ዋቢ ቡርቃ በበኩሉ በህክምና ወቅት የአያያዝ ችግር እንደነበረበት አስረድቷል።

ግራ ቀኙን ያዳመጠው ችሎቱ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ በአግባቡ መስራቱን እንደተገነዘበ ገልጿል።

የዋቢ ቡርቃን በህክምና ወቅት የነበረውን አያያዝ በተመለከተ በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ማጣራት አድርጎ የነበረውን አያያዝ በተመለከተ ፖሊስ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ አዟል።

ጠበቆች የጠየቁት አቤቱታ አስተዳደራዊ ስለሆነ ለሬጅስትራር እንዲያቀርቡ ታዟል።

መርማሪ ፖሊስ ቀሪ የምርመራ ስራዎችን አጠናቆ ለነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ 12 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም