የኢትዮ-ሕንድ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ተጀመረ

62
አዲስ አበባ ግንቦት  1/2010 ሁለተኛው የኢትዮ-ሕንድ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ዛሬ በኒውዴልሂ ተጀምሯል። በስብሰባው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተመራ የልዑካን ቡድን መገኘቱን የሚኒስቴሩ የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል። ዶክተር ወርቅነህ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት ወደ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንዲያድግ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮ-ሕንድ የሚኒስትሮች የጋራ ስብሰባ እስከ ነገ ድረስ የሚቆይ ይሆናል። በፖለቲካ ፣ በአካባቢያዊ እና በዓለም አቀፍ የሠላም እና ደህንነት ጉዳዮች እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትብብር ዙሪያ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል። የሕንድ መንግስት ኢትዮጵያን በአቅም ግንባታ መስክ ይደግፋል፤ ሕንድ በቀጣይም በህዋ ሳይንስ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላት ተጠቁሟል። ከጋራ ኮሚሽኑ ስብስባ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ተቋማትን ለመደገፍ ስምምነት ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል። የመጀመሪያው የኢትዮ-ሕንድ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2010 በኒውዴልሂ መካሄዱ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያና ህንድ ታሪካዊ ግንኙነት የሚጀምረው በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን በዛው ወቅት የሁለቱ አገራት ዜጎች የንግድ ልውውጥ ያደርጉ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። አገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1948 ነው። የኢትዮጵያና ሕንድ የንግድ ልውውጥ መጠን ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የደረሰ መሆኑንና በኢትዮጵያ ፈቃድ የተሰጣቸው 427 ኩባንያዎች ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ማፍሰሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ምህንድስና፣ ግብርና፣ መድሐኒት፣ ሆቴልና ሬስቶራንት እንዲሁም የአበባ ልማት የሕንድ ኩባንያዎች የተሰማሩባቸው ዘርፎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም