መገናኛ ብዙሃን ስለ ኮቪድ-19 ከተለመደው ወጣ ያሉ ዘገባዎችን መስራት አለባቸው

109

አዲስ አበባ  ነሐሴ 01/2012(ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን ኮቪድ-19ን ለመከላከል ከተለመደው የዘገባ ዘይቤ በመውጣት ኅብረተሰቡን በተሻለ በሚያስተምሩ አዘጋገቦች ላይ ማተኮር አለባቸው ተባለ።

ይህን ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መገናኛ ብዙሃን ኮቪድ-19 በኅብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት የመቀነስ ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ቫይረሱ እያደረሰ ካለው ጉዳት አንጻር ኅብረተሰቡ ከተለመደው የአኗኗር ዘይቤው እንዲወጣና የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እንዲተገብር ለማድረግ የዘገባው አይነት ወጣ ማለትን ይጠይቃል።

ኅብረተሰቡ በሚረዳበትና አስተማሪ በሆኑ የግለሰብ ታሪኮች ላይ በመመርኮዝ በቂ ግንዛቤ ይዞ መከላከል ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይገባል ነው ያሉት አቶ ንጉሱ።

በተከሰተው መዘናጋት ኅብረተሰቡ ለሞትና ለሌላም ጉዳት እየተዳረገ በመሆኑ መገናኛ ብዙሃኑ የበለጠ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

አቶ ንጉሱ የሚዲያው አመራርና ጋዜጠኞች ስለ ቫይረሱ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ለኅብረተሰቡ በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ግን አልሸሸጉም።

ራሳቸውን ለጉዳት በማጋለጥ ኅብረተሰቡን በማስተማር ተግባር ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፤ ለዚህም እውቅና ይገባቸዋል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ ስለ ቫይረሱ በቂ ግንዛቤ ቢኖረውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳየ ባለው መዘናጋት የቫይረሱ ስርጭትና በዚህ ሳቢያ የሚሞተው ሰው ቁጥር መጨመሩንም አክለዋል።

ይህ እንደ አገር ከፍተኛ ስጋት የሆነበትና የበለጠ መስራት የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለተጀመረው አገራዊ ንቅናቄ መገናኛ ብዙሃኑ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ጉዳቶችን ለመቀነስ መረባረብ አለባቸውም ብለዋል።

በአገሪቷ ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር በሚተገበረው የማኅበረሰብ ንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ምርመራ እንደሚደረግላቸው ተነግሯል።