በሆሳዕና ከተማ ለችግር ለተጋለጡ ለ200 ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

37

ሆሳዕና ነሀሴ 1/2012 (ኢዜአ) የዋቸሞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የበጎ አድራጎት ማህበር በኮሮና ምክንያት በሆሳዕና ከተማ ለችግር ለተጋለጡ 200 ወገኖች የምግብ ድጋፍ አደረገ።

በድጋፍ አሰጣጥ ስነ ስርዓት የተገኙት የሀድያ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ርዮተ አለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደግነህ አባተ ማህበሩ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው መንግስት ብቻውን የሚያከናውነው ነገር እንደሌለ ህብረተሰቡ በመረዳት የተቸገሩ ወገኖችን ማገዝ እንዳለበትም አመልክተዋል።

የዋቸሞ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ታምሬ ኮራሴ በበኩላቸው የበጎ አድራጎት ማህበሩ በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ለመደገፍ የተቋቋመ መሆኑን ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱ በሀገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል  ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የማህበሩ ሰብሳቢ መምሀር ጫኬቦ ቤይካሶ  ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በኮሮና ምክንያት ሰርተው መብላት ለማይችሉ 200 አቅመ ደካሞች ከ700ሺህ ብር በላይ በማውጣት በነፍስ ወከፍ ሰላሳ ኪሎ ግራም የስንዴ ዱቄትና አንድ ሊትር ዘይት ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የሴች ዱና ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መስከረም ቡባሞ በሰጡት አስተያየት  የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የተለያዩ የቀን ስራ ሲያከናውኑ እንደነበሩ አስታውሰው የኮሮና  መከሰቱን ተከትሎ መስራት እንደተቸገሩ ተናግረዋል።

ማህበሩ ባደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውንና ይህም መስራት እስኪችሉ ድረስ ፍላጎታቸው መሆኑን   ገልጸዋል፡፡

በሆሳዕና የአራዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መሰረት ተሰማ በበኩላቸው ልብስ በማጠብ ሶስት ልጆቻቸውን ያለ አባት እንደሚያሳድጉ ገልጸው የኮሮና ወረርሽኝ በመከሰቱ ስራቸውን ለማቆም በመገደዳቸው ተችገረው መቆየታቸውን አመልክተዋል።

ለተደረገላቸውም ድጋፍ አመስግነዋል።