ከመደመር መፅሃፍ ሽያጭ የተገኘ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ለቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት ተበረከተ

72

አዲስ አበባ  ነሐሴ 01/2012(ኢዜአ) ከመደመር መፅሃፍ ሽያጭ የተገኘ 110 ሚሊዮን 671 ሺህ ብር ለትምህርት ቤት ማሰሪያ እንዲውል ለቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት ተበረከተ።

መደመር መጽሃፍ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጻፈና የኢትዮጵያ መጻዒ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዞ ምን መሆን እንዳለበት የሚያትት ነው።

በመጽሃፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በገጠሪቷ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ትምህርት ቤት ለማሰራት እንደሚውል በመጽሃፉ የመጀመሪያ ገጽ ተጠቅሷል።

በዚሁ መሰረትም የመጽሃፉ ደራሲ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሽያጩ የተገኘውን 110 ሚሊዮን 671 ሺህ ብር ዛሬ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አበርክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከለጋሾች ገንዘብ በማሰባሰብ በሁሉም የአገሪቷ ክልሎች 20 ትምህርት ቤቶችን ማስገንባቱን ተናግረዋል።

ከተገነቡት ትምህርት ቤቶች መካከልም የተወሰኑት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ነው ያሉት።

ከዚህ አንጻር ጽህፈት ቤቱ ያለውን ልምድ በመጠቀም በሁሉም የአገሪቷ ክልሎች ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች እንዲያስገነባ ከመጽሃፍ ሽያጭ የተገኘው ገቢ እንዲሰጠው መወሰኑን አውስተዋል።

የ"መደመር" እሳቤ ኢትዮጵያን ከገጠማት ሰውና መዋቅራዊ ወለድ ስብራቶች ጠግኖ ወደ ብልጽግና ማማ መውጣት መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

በዚህ ረገድ ከመጽሃፉ የተገኘው ገቢ ለማኅበረሰብ ልማት እንዲውል መደረጉን አብራርተዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ትምህርት ቤቶቹን በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚገነባም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከመጽሃፉ ሽያጭ የተገኘው ገቢ ከክልል ክልል እንደሚለያይም ተናግረዋል።

በመሆኑም ክልሎች መጽሃፉን በመግዛት ባላቸው ድርሻ ልክ ትምህርት ቤቶች ይገነቡላቸዋል ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የትምህርት ቤቶች ግንባታ ሂደቱን በቅርበት እንደሚቆጣጠርም ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተፃፈውና 16 ምዕራፎች ያሉት መደመር መፅሃፍ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሃብትና በውጭ ግንኙነት መስኮች ምን መልክ ሊኖራት እንደሚገባ የጠቆመ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም