ምርት ገበያው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 40 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን አገበያየ

71

አዲስ አበባ፣ነሀሴ 1/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገቢያ በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት 40 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ከ761 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የሆኑ ምርቶችን ማገበያየቱን አስታወቀ።
በዚህም የዕቅዱን 99 በመቶ፤ በገቢ ረገድም 113 በመቶ ማሳከቱን የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘው ነገራ ተናግረዋል።

ክንውኑ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በግብይት መጠን 12 በመቶ፤ በግብይት ዋጋ መጠን ደግሞ በ18 በመቶ ጭማሪ እንዳለውም ገልጸዋል።

አቶ ወንድማገኘሁ እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግብይት ከተካሄደባቸው ምርቶች ውስጥ ቡና 40 ነጥብ 5 በመቶ፣ ሰሊጥ 34 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ አላቸው።

እንደዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ግብይታቸው በምርት ገበያ ብቻ እንዲከናወን ከተደረጉት ምርቶች መካከል በአረንጓዴ ማሾ ከዕቅድ በላይ ለማከናወን ተችሏል።


"በበጀት ዓመቱ 308 ሺህ 303 ቶን ቡና በ24 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር፣ 262 ሺህ 99 ቶን ሰሊጥ በ11 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር፣ 78 ሺህ 208 ቶን አኩሪ አተር በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ማገበያየት ተችሏል" ብለዋል።


በተጨማሪም 59 ሺህ 210 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ1 ነጠብ 6 ቢሊዮን ብር፣ 47 ሺህ 825 ቶን ነጭ ቦለቄ በ1 ነጥብ 04 ቢሊዮን ብር፣ 6 ሺህ 259 ቶን ቀይ ቦለቄ በ103 ሚሊዮን ብር ግብይት መከናወኑን አመልክተዋል።


እንደ አቶ ወንድማገኘው ገለጻ ምርት ገበያው ባለፉት 12 ዓመታት 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምርት በ275 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል።

ባለፉት ዓመታት ለአገሪቱ የውጭ ንግድ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት መዘርጋት እንደተቻለም ገልጸዋል።


በዚህም ምርት ገበያው የአገልግሎት አድማሱን የማስፋት፣ የሚያገበያያቸውን ምርቶች መጠን የመጨመር፣ ቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅሙን የማሳደግ፣ ወደ አርሶ አደሩ ይበልጥ በመቅረብ አገልግሎት የመስጠትና አዳዲስ አሰራሮችን የመዘርጋት ሥራ መሰራቱን ነው የገለጹት።


በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አርሶ አደሮች ምርታቸውን በምርት ገበያው መጋዘኖች በማከማቸት ከባንኮች ብድር የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱንም አቶ ወንድማገኘው ተናግረዋል።


እንደእሳቸው ገለጻ በበጀት ዓመቱ ካገጠሙ ችግሮች መካከል በዓለም ላይ የቡና፣ የቅባትና ጥራጥሬ ምርቶች ዋጋ መቀነስ የሚጠቀስ ነው።

የቀይ ቦለቄ ግብይት በምርት ገበያ በኩል እንዲካሄድ ቢደረግም ህግ ወጥ ንግድ እንቅፋት መሆኑንም አመለክተዋል።

"በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ በዓለም ገበያ የዋጋ መዋዠቅ እና የኮንትሮባንድ ንግድ የገጠሙ ተግዳሮቶች ናቸው" ብለዋል።

በ2013 በጀት ዓመት የርግብ አተር፣ ዥንጉርጉር ቦሎቄና የጥጥ ግብይት ለመጀመር መታሰቡን ገልጸው፣ እነዚህ አዲስ የሚገቡ ምርቶችን ጨምሮ 784 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምርት በዓመቱ ለማገበያየት መታቀዱን ጠቁመዋል።

ሰሊጥና አኩሪ አተርን በግብዓትነት በመጠቀም ዘይት ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች አዲስ የግብይት መስኮት በመክፈት አገልግሎት ለመስጠትና ባሉት ቅርጫፎች ተጨማሪ ምርቶች ለመቀበል ዝግጅት መደረጉንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።


በቡሌ ሆራ፣ መቱና ቴፒ የተገነቡት አዳዲስ መጋዘኖች አብዛኛው የግንባታ ሥራቸው የተጠናቀቀ በመሆኑ በተያዘው በጀት ዓመት ሥራ የማስጀመር ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

"በዘመናዊ የግብይት ስርዓቱ የቅመማ ቅመምና የማዕድን ዓይነቶችን ለይቶ ወደግብይቱ ለማስገባት ጥናት ይካሄዳል" ብለዋል።


ከዚህም በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ የላቦራቶሪ አገልግሎትን አውቶሜት ማድረግና የተለያዩ ዘመናዊ አሰራሮችን የማጠናከር ሥራ እንደሚሰራም ነው ያመለከቱት።


ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልገሎት ለማስፋት የአርሶ አደሩንና የህብረት ሥራ ማህበራትን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል።

ተጫማሪ አባላትና ቀጥታ ተገበያዮችን የመመልመል ሥራና ሌሎች የደንበኞች እርካታን የሚፈጥሩ ተግበራትን ለማከናወን ዕቅድ መያዙንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም