የአፋር ክልል ምክር ቤት አስረኛ መደበኛ ጉባኤ በመጪው እሁድ ይጀመራል

66

ሰመራ ነሐሴ1/2012 (ኢዜአ) የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን አስረኛ መደበኛ ጉባኤ በመጪው እሁድ በሰመራ ከተማ እንደሚጀመር የምክር ቤቱ ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አሚና ሴኮ አስታወቁ።

ወይዘሮ አሚና እንደገለጹት የምክር ቤቱ ጉባኤ  የህዳሴ ግድቡ ውሃ ሙሌት በስኬት በተጠናቀቀበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑ ከሌላው ጊዜ የተለየ ያደርገዋል።

ጉባኤው ለሶስት ቀናት  በሚያደርገው ቆይታ  ከሚመክርባቸው አጀንዳዎች መካከል የክልሉን አስፈጻሚ አካላት የ2012 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም፣ የዋና ኦዲተርና የጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ ሪፖርት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

በኮሮና መከላከልና አረንገጓዴ አሻራ ስራዎች  እንዲሁም በወቅታዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የምክር ቤቱ ጉባኤ የሚወያይባቸው ሌሎች አጀንዳዎች ናቸው።

በመጨረሻም ጉባኤው የ2013 ስራ ዘመን የክልልን መንግስት የልማት እቅድና ማስፈጸሚያ   በጀት በማጽደቅ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የአፋር ክልል ምክር ቤት 96 አባላት እንዳሉት ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም