በጅማ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን እናድሳለን - ባለሀብቶች

196

ጅማ (ኢዜአ) ነሐሴ 1/2012 በጅማ ከተማ የሚገኙ ባለሃብቶች በእርጅና የመፈራረስ አደጋ የተጋረጠባቸው ትምህርት ቤቶችን በማደስና አዳዲስ የማስፋፊያ ግንባታዎችን በመስራት ዘርፉን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለፁ ።   

በከተማዋ የሚገኙ ከ200 በላይ ባለሃብቶች በመንግስት ትምህርት ቤቶች አያያዝና አጠበበቅ ላይ ያተኮረ ውይይት ትናንት ከከተማው አስተዳደር ጋር አካሔደዋል ።

ባለሃብቶቹ ከከተማው አስተዳደር ጋር በመሆን ነባር ትምህርት ቤቶችን በማደስና የማስፋፊያ ግንባታዎች በማከናወን የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ።

ከባለሃብቶቹ መካከል የአዌቱ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ባለቤት አቶ አህመድ አባዲኮ እንደገለጹት በከተማችን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በጣሊያን ወረራ ወቅት የተሰሩና ያረጁ በመሆናቸው ለዓይንም ጭምር የማይስቡ ናቸው ።

ይህንን ችግር ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን ጥረት ለማገዝ በተወለዱበት አካባቢ በሚገኙና በተማሩባቸው ሁለት ትምህርት ቤቶች አራት የመማሪያ ክፍሎች ሰርተው ለማስረከብ ቃል ገብተዋል ።

ሁላችንም ተባብረን የአቅማችን አስተዋፅኦ ካደረግን ትምህርት ቤቶቹን ማሻሻል እንችላለን ያሉት አቶ አህመድ ለተማሪዎች ከሚሰጠው የቀለም ትምህርት በተጨማሪ የግብረ ገብነት ትምህርት በትኩረት የሚሰጥበት እድል እንዲመቻች ጠይቀዋል ።

ወይዘሮ ዘይናባ አባ ጆቢር አባ ጅፋር የተባሉ ባለሀበት በበኩላቸው በሚኖሩበትና በተማሩበት የአባ ጅፋር ቤተ መንግስት አጠገብ በሚገኘው ትምህርት ቤት ከእህቶቻቸው ጋር በመሆን ሶስት ክፍሎችን አሰርተው ማስረከባቸውን ተናግረዋል ።

ከተሰሩት መካከል ሁለቱ የመማሪያ ክፍሎች ሲሆኑ አንደኛው ደግሞ ተማሪዎች በዕረፍት ሰዓታቸው ቴሌቪዥን እያዩ የሚዝናኑበት ነው ብለዋል ።

የጅማ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እስማኤል ሱሌይማን ትናንትናና ዛሬ በሚል ርዕስ  የጅማ ከተማን የትምህርት አሰጣጥና የመማሪያ ክፍሎች ሁኔታዎችን የተመለከተ የውይይት መነሻ ሓሳብ አቅርበዋል ።

 በውይይቱ ላይም 20 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች ረጅም ታሪክ ያላቸው ፣ ትውልድን በእውቀት በማነጽ ለአገርና ለወገን ያገለገሉ፤ እንደ ቅርስም ሊታዩ የሚገባቸው ተቋማት መሆናቸውን ተገልጿል፡፡

ትምህርት ቤቶቹ ከዓመታት በፊት በአበባ ያሸበረቁና በዕጸዋት የተዋቡ እንደነበሩ ኃላፊው አስታውሰው በእርጅና በመፈራረስ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ለመማር ማስተማር ስራም አመቺ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ባለሃብቶች ይህን ችግር በመረዳት ከ70 በላይ የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባትና ለማደስ ፈቃደኝነታቸው መግለፃቸውን ኃላፊው ገልፀዋል ።

ከባለሃብቶቹ በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪው ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማስተባበር በ2013 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ከአረጁ፣ ከፈራረሱና ከአቧራ ተላቅቀው በተሻሉ ክፍሎች እንዲማሩ ለማድረግ እንረባረባለን ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም