ኅብረተሰቡ የእጅ ንጽህናና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ በኩል ክፍተት እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

50

አዲስ አበባ  ነሀሴ  1/2012 (ኢዜአ)በአዲስ አበባ ህብረተሰቡ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የእጅ ንጽህናና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ በኩል ከፍተኛ ክፍተት እየታየበት መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስቴር አማካሪ ዶክተር ስንታየሁ ጸጋዬ ሚኒስቴሩ ያደረገውን የአዝማሚያ ጥናትን ተመርኩዘው እንደገለጹት፣ በከተማዋ ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ስርጭት አለ።

እስከ ሐምሌ 29 ቀን 2012 ድረስ በቫይረሱ ከተያዙ 20 ሺህ 336 ሰዎች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት አዲስ አበባ የተገኙ መሆኑንና ከዚህም ውስጥ ቦሌና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ጠቁመዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን በቫይረሱ ሳቢያ እንደ አገር ከተመዘገበው አጠቃላይ ሞትም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመዘገበው በአዲስ አበባ መሆኑን ገልጸዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከልም የከተማዋ ነዋሪዎች ምንም እንኳን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በማድረግ ረገድ አዎንታዊ ለውጥ ቢያሳዩም በሌሎች መከላከያ ስልቶች ላይ ክፍተት አለባቸው ብለዋል።

በተለይም ደግሞ ቫይረሱን ለመከላከል ወሳኝ የሆኑትን የእጅ ንጽህናና አካላዊ ርቅትን መጠበቅ ላይ ከፍተኛ ክፍተት የተስተዋለባቸው መሆኑን ነው ያነሱት።

በመሆኑም ኅብረተሰቡ አሁን የሚያሳየውን መዘናጋት በመተው ወረርሽኙን ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች የሚቀርቡትን ምክረ-ሃሳብ በትክክል ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል።

በክልሎችም አካባቢ ተመሳሳይ ችግሮች መኖራቸውን የገለጹት አማካሪው፣ ኅብረተሰቡ በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ወረርሽኙ ወደኢትዮጵያ ከገባበት መጋቢት ወር ጀምሮ የመጀመሪያዎቹን 1 ሺህ ተጠቂዎች ለማግኘት 79 ቀናት መፍጀቱን አስታውሰው፣ "አሁን ላይ ከሁለት ቀናት በታች የወሰደበት ጊዜ ላይ ደርሰናል" ብለዋል።

በተለይም ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ የተጠቂዎች ቁጥር የተመዘገበበት ወቅት መሆኑንና ይህም ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ እተስፋፋ ስለመሆኑ እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል።

በአገሪቱ እስካሁን አጠቃላይ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል 67 በመቶ የሚሆኑት በሐምሌ ወር ብቻ የተያዙ መሆናቸውን ዶክተር ስንታየሁ ለአብነት አንስተዋል።

በተለይም ደግሞ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ህልፈት ህይወት በኋሏ በተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ መሰራጨቱን ነው ያብራሩት።

"በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ በቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጠቁ አሥር አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች" ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜያት በኋላም የቫይረሱ መስፋፋት ተከትሎ በአገሪቱ የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥርም ከሌሎች አገራት አንጻር አነስተኛ መሆኑን ነው የገለጹት።

ስለዚህም ኅብረተሰቡ የቫይረሱን መስፈፋት ከግምት በማስገባት የሚያደርጋቸውን ጥንቃቄዎች ይበልጥ አጠናክሮ በመቀጠል እራሱንና ማኅበረሰቡን ከኮሮናቫይረስ መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም