የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች የግድቦችን የአገልግሎት ዘመን ለማርዘም ጉልህ ሚና አላቸው ... የዘርፉ ባለሙያዎች

96

አዲስ አበባ  ነሀሴ  1/2012 (ኢዜአ)የተፈጥሮ ሃብትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ለሰው ልጆች ሕልውና ከመሆን ባለፈ የግድቦችን የአገልግሎት ጊዜ ለማርዘም ጉልህ ሚና እንዳላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ገለፁ።

በኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማት መከናወን ከጀመረ እስከ አሁን ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።

የሰው ልጆች ሕይወት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከተፈጥሮ ሃብት ልማት ጋር የተቆራኘ መሆኑንም አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሃብቶቹ በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ሲውሉ መልሰው የማይተኩ ከሆነ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ልጆች አኗኗር ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደራቸው አይቀሬ ነው።

ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ማዕበልና ሰደድ እሣትን የመሳሰሉ ችግሮች መነሻም የተፈጥሮ መዛባት እንደሆነ ነው ባለሙያዎቹ የሚገልጹት።

የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የደን ሽፋን እንደነበር በታሪክ ከመማር ባለፈ ሃብቱን ጠብቆ ማቆየት አልተቻለም።

ለዚህ ደግሞ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የከተሞች መስፋፋት እንዲሁም አገር አቀፍ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖርን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ የሰው ልጆች ያለተፈጥሮ ሃብት ሕይወታቸውን መምራት ከባድ ይሆንባቸዋል።

በሌላ በኩል የተፈጥሮ ሃብትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ለሁሉም አይነት የልማት ስራዎች አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም በተለይ የግድቦችን የአገልግሎት ዕድሜ በማርዘም በኩል ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።

በታሪክ ሲነገር የኖረውን የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ለመመለስ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል።

ዘመቻው በተለይ ተፋሰሶችና ግድቦች ባሉባቸው አካባቢዎች በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው ፕሮፌሰር ፍቃዱ የሚናገሩት።

በ2012 ዓ.ም ችግኞችን በመትከልና ከሰውና እንስሳት ንክኪ በመጠበቅ ከ421 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን የገለጹት ደግሞ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ ናቸው።

ባለስልጣኑ ለግድቦች፣ ለሐይቆችና ለወንዝ ዳርቻዎች ትኩረት በመስጠት የተፋሰስ ልማት ስራዎችን እንደሚያከናውንም ነው የገለጹት።

ይህም ወደ ግድቦች የሚገባው ውሃ ንጹህና የተመጣጠነ ለማድረግና የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ ያስችላል ነው ያሉት።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የዓባይ ተፋሰስን ጨምሮ ግድቦች ባሉባቸው ቦታዎች ከግድብ ግንባታ ጎን ለጎን የተፋሰስ ልማት ስራዎችንም ያከናውናል ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጥ በተለይ በላይኞቹ ተፋሰሶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች በደን እንዲሸፈኑና እንዲያገግሙ ይደረጋልም ብለዋል።

ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የዓባይ ተፋሰስን ጨምሮ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ በአገሪቷ በተለይም በተፋሰሶች ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ቀደም ሲል ከነበረው አኳያ የተሻለ ቢሆንም አሁንም ቀሪ ስራዎች አሉ።

ፕሮፌሰር ፈቃዱ የአካባቢ ጥበቃ ስራ የአንድ ተቋም ብቻ መሆን እንደሌለበትና የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ርብርብ እንደሚጠይቅ ነው ያስገነዘቡት።

በኢትዮጵያ የተመናመነውን የደን ሃብት ለመመለስ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በ2011 ዓ.ም በመላ አገሪቷ የተለያዩ ሥፍራዎች አራት ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል።

በ2012 ዓ.ም አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል በታቀደው መሰረትም አገራዊው ዘመቻ እየተከናወነ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም