በጌዴኦ ዞን ከእቅድ በላይ ገቢ ተሰበሰበ

55

ዲላ ኢዜአ ነሐሴ 1 / 2012 ዓም  በጌዴኦ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 463 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ ማሳካቱን የዞኑ ገቢዎች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ገለፀ ። 

የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት አየለ እንደገለፁት ገቢው የተሰበሰበው ከቀጥታና ቀጥታ ካልሆነ ታክስ እንዲሁም ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ነው ።

በበጀት ዓመቱ 443 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 20 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ።

ገቢው ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው ብለዋል ።

በየደረጃው ያለ የገቢ ዘርፍ አመራርና ባለሙያ ተናብቦ መስራቱና በግብር ከፋዩ ዘንድ ግብር የመክፈል ባህል እየዳበረ መምጣቱ ለገቢው ማደግ ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን ገቢው ከእቅድ አንጻር የተሻለ ቢሆንም የዞኑ አቅም የሚያመነጨውን ኢኮኖሚ ያክል ለመሰብሰብ ገና ብዙ መስራትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በአዲሱ ዓመት ሁሉንም አቅሞች በማስተባበር ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

የኮሮና ቫይረስ መከሰት የንግድ እንቅስቃሴውን በማቀዝቀዙ የገቢ ስራ ላይ ጫና እንደሚያሳደር የሚናገሩት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አታራ ናቸው።

የዲላ ከተማ ሙሉ ወጪ በራሷ ገቢ የሚሸፈን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኮሮና ተጽዕኖን በመቋቋም የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ አንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስን ተከትሎ መንግስት ውዝፍ እዳ ስረዛ ማድረጉ ፍሬ ግብራችንን በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ወስጥ እንድንከፈል መነሳሳትን ፈጥሯል የሚሉት ደግሞ በዞኑ ይርጋጨፌ ወረዳ የቡና ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ በረከት ተሰማ ናቸው።

ምንም እንኳን የወረሪሽኙ መከሰት በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ያሳደረ ቢሆንም የሚጠበቅባቸውን ግብር ከመክፈል እንዳላገዳቸው ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ አስቻለው በቀለ በይርጋጨፌ ከተማ በሆቴል ስራ ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸው የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ገበያው ከወትሮ መቀዛቀዙን ጠቅሰው ይሁንና ሁኔታውን ከግምት ውስጥ ያስገባ ግብር መክፈላቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም