በጠንካራ ዕሴት የተገነባው የህዝቦች አንድነት በጸረ-ሰላም ኃይሎች ሙከራ አይፈርስም…የደቡብ ክልል ምክር ቤት

51

ሀዋሳ (ኢዜአ) ነሐሴ 1/2012 ለውጡን የማይፈልጉ ሀይሎች ለዘመናት በህዝቦች ጠንካራ ዕሴት የተገነባውን አንድነት ለመሸርሸር እየሰሩ ቢገኙም ጥረታቸው አይሳካም ሲሉ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ሔለን ደበበ ገለጹ። 

የክልሉ ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔኤውን በሃዋሳ ከተማ ማካሄድ ጀመሯል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ አፈ-ጉባኤዋ እንደገለጹት በመላው ሃገሪቱ የመጣውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ የማይፈልጉ ኃይሎች በህዝቦች መካከል ጸንቶ የኖረውን የአብሮነት እሴት ለመሸርሸር የሚያደርጉት ጥረት አይሳካም ።

ጉባኤው የህዝቦችን የዘመናት ጥያቄ ለመመለስ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የሚያስችል መነቃቃትና የይቻላል ስሜት የፈጠረው የመጀመሪያው የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተጠናቀቀበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል።

"ለውጡን ጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆምና የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ የምክር ቤቱ አባላት የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣት አለባቸው"ብለዋል።

ዴሞክራሲን በማስረጽ ዜጎች ለዘመናት የተመኙትና የናፈቁትን ተስፋ ለውጡ ይዞ የመጣ በመሆኑ በሀሳብ የበላይነት ከመተማመን በቀር ''የእኔ'' ብቻ የሚለው አተያይ ሊታረም የሚገባ ነውም ብለዋል።

የህዝቦች አንድነት ከመዋቅር ጥያቄ በላይ መሆኑን በመረዳት ለዘላቂ ተጠቃሚነት እርብርብ ማድረግ ከየትኛውም ውሳኔ መቅደም የሚገባው መሆኑን በማስገንዘብ መንግሥትም የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ለሶስት ቀናት የሚቆየው ጉባኤው በ2012 በጀት ዓመት የክልሉ መንግስት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ የ2013 ስራ ዘመን ዕቅድንና ማስፈጸሚያ በጀት ላይ በመወያየት እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ጉባኤው በተጓደሉ የካቢኔ አባላት ምትክ አዳዲስ አመራሮችን ይሾማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም