የሰላምና የጸጥታ ችግር ለኢንቨስትመንት ስጋት ሆኗል ... ኮሚሽኑ

78

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 30/2012 ( ኢዜአ) የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ መፍትሔ ካላገኘ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ የ2012 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2013 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከክልል ኢንቨስትመንት ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።

ኢንቨስትመንት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ዋነኛ አስተዋጽኦ ከሚያበርክቱ ዘርፎች አንዱና ዋነኛው ነው።

ይሁንና በየወቅቱ የሚከሰቱ የሰላምና የጸጥታ ችግሮች ለዘርፉ እንቅስቃሴ ስጋት ሆኗል።

በውይይት መድረኩም አይነተኛ ትኩረት የነበረው በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚከሰት ግጭትና አለመረጋጋት የሚደርሰው ውድመት ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ስጋት መሆኑን ነው።

የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዋሲሁን ጎልጋ እንዳሉት በክልሉ በሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች ኢንቨስትመንቱ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ባለሀብቶችን እያሰጉ መጥተዋል።

አለመረጋጋቱ በኢንቨስትመንት ሥራው ላይ መስተጓጎል በመፍጠር ዘርፉን መቀላቀል የሚፈልጉ አዳዲስ ባለሀብቶችን ፍላጎት እንደሚቀንስም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ ወንድምአገኘሁ በበኩላቸው፣ በየጊዜው የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች በኢንቨስትመንት መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ችግሩ ኢንቨስትመንት እንዲሸሽ የሚያደርግ በመሆኑ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የውሃ፣ መብራት፣ መንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በኢንቨስትመንት ተቋማት ውስጥ በሚፈለገው ሁኔታ እየቀረቡ አለመሆኑ የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የደቡብ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሥራት አሰፋ እንደገለጹት፣ የሰላምና የጸጥታ ችግሩ ኢትዮጵያ በሚፈለገው መጠን ከኢንቨስትመንት አቅሟ ተጠቃሚ እንዳትሆን የሚያደርጋት ነው ብለዋል።

ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸውና ለዚህም የጋራ ሥራ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የመሬት አቅርቦት መጓተት፣ ያልተደራጀ የመረጃ አያያዝ፣ በኢንቨስትመንት መስኩ ያለው ደካማ ቅንጅታዊ አሰራር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በዘርፉ ላይ ያለው የአመለካከትና አመራር የመስጠት ችግርና ሌሎችም በውይይቱ ተሳታፊዎች የተነሱ ሐሳቦች ናቸው።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ የሰላምና የጸጥታ ችግርን ለመፍታት የኢንቨስትመንት ተቋማትን የሚጠብቅ የጸጥታ አካል የማሰማራትና ህብረተሰቡን አሳታፊ ያደረገ ጥበቃ የማድረግ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችሉ ሥራዎችን እንደሚያከናውንና የክልል ኢንቨስትመንት ተቋማት አመራሮችም በየክልሉ ከሚገኙ የጸጥታ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የክልል ኢንቨስትመንት ተቋማት አመራሮችም መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ ባለሀብቶች በየጊዜው በማነጋገር የሚያጋጥማቸውን ችግሮች መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በዘላቂነት የሰላምና የጸጥታ ችግሩን ለመፍታት የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ነው ያሉት።

በተሳታፊዎች የተነሱ የዘርፉ ተግዳሮቶች ኮሚሽኑ በሂደት እየፈታቸው እንደሚሄድና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በተናጠል ከመጓዝ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም