በሐረሪ ክልል በህገወጥ መንገድ የተያዙ መሬት እና ቤቶችን ማስመለስ ተጀመረ

71

ሐረር፣ ሐምሌ 30/2012 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ መሬት እና ቤቶችን የማስመለስ ስራ መጀመሩን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ናስር ዩያ  ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ  የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ጥረት ሲደረግ ቢቆይም በነበረው ክፍተት በርካታ ቤቶችና መሬት  በህገ ወጥ ግለሰቦች ተይዘዋል።

ቢሮውም በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እና ህዝቡ ያለ ስጋት እንዲኖር ለማስቻል በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ መሬትና  ቤቶችን የማስመለስ ስራ ጀምሯል ብለዋል።

በክልሉ በህገ ወጥ መንገድ ከተያዙት መካከል የቀበሌ፣ የቁጠባ ቤቶችና የኢንቨስትመንት መሬት ይገኝበታል።

ቢሮው ከክልሉ ከተማ ልማት፣ቤቶች ኤጀንሲ፣የፍትህና የጸጥታ ኃይል ጋር በመጀመሪያው ዙር ባከናወነው ስራ በዘጠኝ ስፍራ የኢንቨስትመንት መሬት፣ ስምንት የቀበሌና ቁጠባ ቤቶች  ከህግ ወጦች ላይ እንዲመለሱ መደረጉን አስታውቀዋል።

ህገ ወጥ መሬትና ቤት ይዘው የተገኙ ሩ 18 ሰዎች በቁጥጥር  ስር መዋላቸውንም አመልክተዋል።

በተለይ የሐረር ከተማ ፕላን እንዳይኖራት የተከናወኑ ህገ ወጥ የቤት ግንባታዎች ላይ በቀጣይ ህግን የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

በዚህ ህገ ወጥ ተግባር  ስራ ላይ የተሰማሩ የመንግስት አካላት፣ደላሎችና ሌሎችም ግለሰቦች  በቁጥጥር ስር ለማዋል ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልሃኪም አብዱማሊክ  በበኩላቸው "ባለፉት ሁለት ዓመታት በሐረሪ ገጠርና ከተማ  268 ሄክታር መሬት በህገ ወጥ መንገድ ተወሯል፤10 ሺህ የሚጠጋ ህገ ወጥ የቤት ግንባታም ተከናውኗል፤ በርካታ የቀበሌና የመንግስት ቤቶችም አለአግባብ ተይዘዋል"ብለዋል።

መሬት በህገ ወጥ መንገድ ከተያዘባቸው መካከል ትምህርት ቤቶች፣ የማዕድን ስፍራዎች ፣የኢንዳስትሪ ዞን፣ ለህዝብ እና ለኢንቨስትመንት አገልግሎት የሚውሉ ቦታዎች  እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣አቃቢ ህግና ፖሊስ  በመቀናጀት የህግ የበላይነትን ለማስከበር በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የመንግስትና ህዝብ ቤቶችን የማስመለስ ስራና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስረድተዋል።

ኃላፊው እንዳብራሩት በተለይ ለምስራቅ ኢትዮዽያ አገልግሎት እንዲሰጥ የተገነባውና በህገ ወጦች ተይዞ የነበረው የአፈር መመርመሪያ ላብራቶሪ መመለሱንና ሌሎችም የኢንቨስትመንት ስፍራዎችን የማስከበር ስራ እየተካሄደ ነው።

በክልሉ በህገ ወጥ መንገድ የተያዘን መሬትና ግንባታን የማስቆሙ ስራ  ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

የከተማው ነዋሪ  አቶ ሐፊዝ አብዱላሂ በሰጡት አስተያየት "የክልሉ መንግስት የጀመረውን ህግን የማስከበር ስራዎች በሌሎችም የወንጀል ድርጊቶች ላይ አጠናክሮ  መቀጠል አለበት " ብለዋል።

በህገ ወጥ ግለሰቦች የተያዙ መሬትና  ቤቶችን የማስመለስ ስራ ቢዘገይም በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ የሚገኘው ህግን የማስከበር ስራ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አሸናፊ ሀብታሙ ናቸው።

በተለይ በዚህ ህገ ወጥ ስራ የተሳተፉትን የመንግስት አካላትም ሆነ ደላሎችን ለመቆጣጠር የተጀመረው ስራ መቀጠል እንዳለበትም  አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም