ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት 100 ቀናት በዲፕሎማሲያዊ መስክ በርካታ ስኬት አስመዝግበዋል

112
አዲስ አበባ  ሀምሌ 4/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ባለፉት 100 ቀናት በውጭ ግንኙነትና በዲፕሎማሲ መስኮች በርካታ ስኬት ማስመዝገባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም  ዛሬ በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባከናወኗቸው ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት ስኬት አስመዝግበዋል ብለዋል። በተለይም ከኤርትራ ጋር የተደረሰው ስምምነት አገራቱ ላለፉት 20 ዓመታት የነበራቸውን አለመግባባት በማስወገድ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲመሰርቱ ያስቻለ መሆኑን ነው ቃል አቀባዩ ያስታወቁት። "ኢትዮጵያና ኤርትራ ያለሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በመካከላቸው ለሁለት አስርት ዓመታት  የቆየውን ልዩነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጥበብ እርቅ እንዲወርድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው" ብለዋል። በዶክተር ዓብይ የሰላም ጥሪ መሰረት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ያሳዩት በጎ ምላሽ እና ሁለቱ መሪዎች በአስመራ የጋራ የሰላም ድንጋጌ መፈረማቸው ትልቅ ስኬት መሆኑንም አውስተዋል። ይህም የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ፍላጎት ከግምት ያስገባ መሆኑን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ "ክስተቱ ሁለቱም አገራት አሸናፊ መሆናቸውን የሚገልፅ ሂደት ነው" በማለትም ተናግረዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት ከኤርትራ ጋር የተደረሰው ስምምነት የምስራቅ አፍሪካን የፖለቲካ ሁኔታ በአዎንታዊ መልኩ በመቀየር ለሌሎችም የአፍሪካ አገራት በምሳሌ የሚጠቀስ እርምጃ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ዶክተር ዓብይ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ተፋላሚ የሆኑትን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና ተቀናቃኛቸው ሬክ ማቻር ከአራት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ በአካል ተገናኝተው እንዲመካከሩ ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ መሪ መሆናቸውንም ገልፀዋል። በተመሳሳይ ለዜጎች ክብር በመስጠት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በሄዱባቸው የጎረቤት አገራት በተለያዩ ምክንያቶች እስር ላይ የነበሩ ሶስት ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን እስረኞችን በማስፈታት ወደ አገር ቤት እንዲመሉ ማድረጋቸውም ትልቅ ስኬት መሆኑን አቶ መለስ አመልክተዋል። ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከግብጽና ከሱዳን ጋር መተማመን እንዲፈጠር ይደረግ የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማስቀጠላቸውም ሌላው ስኬት መሆኑን አንስተዋል። የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በተመለከተም ባለፉት 100 ቀናት የተለያዩ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አቶ መለስ አስታውቀዋል። ከዚህ አኳያ በተለይ ከአሜሪካ ከተለያዩ ኩባንያዎች የተውጣጡ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። የመካከለኛው ምስራቅና እሲያ አገራት ባለኃብቶችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ለማድረግ የሚያስችሉ ጥረቶች መጠናከራቸውን አስረድተዋል። በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵየዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ለማነጋገር በዚህ ወር መጨረሻ ለመጓዝ የታቀደውም ባለፉት የዶክተር ዓብይ የስልጣን ጊዜያት መሆኑን ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእነዚሀ ቀናት ያከናወኗቸው ተግባራት ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም