ሃገርን ለማፍረስ የሚሰሩ የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ሴራ እናከሽፋለን …የአርሲ ዞን ወጣቶች

105

አዳማ ፤ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ)ሃገርን ለማፈራረስ የሚሰሩ የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ የአርሲ ዞን ወጣቶች ገለጹ።

ከአርሲ ዞን 26 ወረዳዎችና የአሰላ ከተማን ጨምሮ ከሶስት የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ወጣቶች የተሳተፉበት የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ ዛሬ በአሰላ ከተማ ተካሒዷል። 

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ከማል ኑጉሴ “ሀገሪቷን ለማስቀጠል እኛ ወጣቶች በአንድነት ሆነን የጥፋት ሃይሎችን እንታገላለን ” ብሏል።

“ወጣቶች በስሜት ተነሳስተን ጥፋት በማስከተል ሳይሆን በተማረ ጭንቅላት ብቻ ታግለን ማሸነፍ አለብን እንጂ መንገድ በመዝጋት፣የዜጎችን ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም አንድም ለውጥ አይመጣም” ብሏል።

ለመንግስት የሚቀርብ ጥያቄ ቢኖር እንኳን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከርና በመወያየት መፍታት እንደሚቻል ገልጾ፤ በክልሉ የተፈፀመው ተግባር ቄሮንም ሆነ ኦሮሞን እንዲሁም ማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍል የማይወክል መሆኑን ተናግሯል።

“ውጭ ቁጭ ብለው መንገድ ዝጉ፣ በገበያ ላይ አድማ አድርጉ፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አግቱ ብለው ትዕዛዝ የሚያስተላልፉ አካላት በተመቻቸ ኑሮ ላይ ሆነው የደሃ ልጆችን ያስቀጥፋሉ ከትናንትናው ህወሃት በምንም አይሻሉም” ብሏል።

“የኦሮሞ ህዝብ በባህሉ ሌላውን ብሔር በጉዲፈቻና ሞጋሳ ወደ ራሱ በማምጣት አቃፊነትን መቻቻልና አብሮነትን ያስተማረ ነው” ያለው ደግሞ ወጣት ሙሐመድ ተሲ ነው።

“እኛ የኦሮሞ ወጣቶች ሀገር ማፍረስ ሳይሆን ከአባቶቻችን በወረስነው ጀግንነትና አንድነት ሀገሪቷን ገንብተን ማለፍ ነው” ብሏል።

ሌላኛው አስተያያት ሰጪ ወጣት ድሪባ ኑጉሴ በበኩሉ “በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው ከውጭ ጠላት ጋር የሚሰሩ፣የጥፋት መመሪያ የሚያስተላልፉ አመራሮች በህግ መጠየቅ አለባቸው” ብሏል።

“የኦሮሞ ህዝብ መቻቻልና አብሮነትን ከገዳ ስርዓት ነው የተማረው” ያለው ወጣት ድሪባ “ወጣቶች በተደላደለ ህይወት ውስጥ ቁጭ ብለው ትዕዛዝ የሚሰጡትን ሃይሎች መስማት የለባቸውም” ብሏል።

የአሰላ ከተማ ከንቲባ አቶ ገብሬ ዑርጌሶ በበኩላቸው የከተማዋ ወጣቶች ንብረት እንዳይወድም ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

ጥቂት ሰዎች የጥፋት ተልእኮ ተቀብለው ሀገር የመበጥበጥ ዓላማ እንዳላቸው ወጣቶች የተረዱበት መድረክ መሆኑንም ጠቅሰው ወጣቶች ጥፋትን ከመከላከል ባለፈ የአፍራሽ ተልዕኮ አስፈፃሚ እንዳይሆኑ የእናትና አባታቸውን ንብረትና ባህል እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

የአርሲ ዞን አስተዳደር አቶ ጀማል አሊይ እንደገለጹት የትራንስፖርት፣የንግድና የገበያ እንቅስቃሴ እንዳይኖር የሚያደርጉ የጥፋት ሃይሎች በወጣቱ ዘንድ ቦታ እንደሌላቸው ከመድረኩ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት መመለሱንም ተናግረዋል።

ወጣቶች መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከጀመረው በጎ ተግባር ጎን እንደሚቆሙ ማረጋገጣቸውን የገለጹት አቶ ጀማል፤ ንብረት በማውደምና በማቃጠል የሚገኝ ውጤት ባለመኖሩ በሰላም ማስፈን ላይ አሁንም ተባብረው መስራት እንደሚገባቸው አስገዝበዋል።

መድረኩን የመሩት የመለስ ዜናዊ አካዳሚ ፕሬዘዳንት አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው መንግስት የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥና አጥፊዎችን ለህግ ከማቅረብ ጎን ለጎን ንብረት የተጎዳባቸውን መልሶ ለማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት የምግብ፣አልባሳት፣የዘርና የአፈር ማደባሪያ ጭምር ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው” ያሉት አቶ አወሉ የዞኑ ማህበረሰብ ተጎጂዎችን በራሱ መልሶ ለማቋቋምና ወደ ቀደመው ህይወት እንዲመለሱ ለማድረግ በየወረዳው ኮሚቴ ተደራጅቶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በድርጊቱ የተሳተፉ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ ከተፎካከሪ ፓርቲዎች ውስጥና በህብረተሰቡ ዘንድም ያሉ የጥፋት ተልእኮ ፈፃሚዎችን ለህግ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ተከትሎ በአሰላ ከተማና በአርሲ ዞን በተፈጠረው ሁከትና ግርግር የሰው ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም የተጠረጠሩ ከ1ሺህ 300 በላይ ግለሰቦች ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም