የድሬዳዋ ተወላጆች ለተቸገሩ ወገኖች 400ሺህ ብር የሚገመት የምግብ ድጋፍ አደረጉ

29

ድሬዳዋ ሐምሌ 29/2012(ኢዜአ) በውጭ የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች በኮሮና ለተቸገሩ ወገኖች 400 ሺህ ብር የሚገመት የምግብ ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉ የተደረገላቸው ለአሰገደችና ለዳዊት አረጋዊያን እንዲሁም በችግር ውስጥ የሚገኙ ህጻናትን ለሚንከባከቡ ሁለት ተቋማት ነው፡፡

ለተቋማቱ ከተሰጡት ድጋፎች መካከል ጤፍ ፣ማሽላ፣ሩዝ ፣ ማካሮኒ ፣ፓስታ፣ወተትና የምግብ ዘይት ይገኙበታል።

ድጋፉን  ያስረከቡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በውጭ የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የማዕድ ማጋራት ጥሪ ተቀብለው ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በተለይ ደግሞ የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ በነበሩት አቶ ተካበ ዘውዴ የሚመራው የዲያስፖራ ኮሚቴ በከተማው የተቸገሩ  ነዋሪዎች በመርዳት ግንባር ቀደም ደራሽ መሆናቸውን አውስተዋል።

ይህ በጎ ተግባር በተለይ በዕለት ምግብ ችግር ትምህርት መከታተል ያልቻሉ ህጻናትን እንዲያማክል አቶ ከድር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የድሬዳዋና የሀገር ወኪል ሆነው እየሰሩ የሚገኙት ዲያስፖራዎች ለሚያከናውኗቸው ተግባራት በሙሉ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

የዲያስፖራዎች ተወካይ አቶ አብዶ ሙሜ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሆኑት ግለሰቦች ከምግብ ድጋፍ በተጨማሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኮሮና መመርመሪያ ማሽን ለመግዛት ገንዘብ ማሰባሰባቸውን ገልጸዋል ፡፡

በሀገር ውስጥ የሚገኙ ባለሃብቶች ከእነዚህ በጎ አሳቢ ዲያስፖራዎች ጋር በመቀናጀት ጀምር ስራቸው እንዲሳካ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋልል፡፡

ድጋፉን ከገኙት  መካከል የአሰገደች ለአረጋዊያን ቋሚ መጦሪያ ተወካይ ወይዘሮ  እመቤት መኮንን ለተደረገላቸው ድጋፍ በአረጋዊያኑ  ስም አመስግነዋል፡፡