በአዲስ አበባ “ቤት ለሁሉም” የተሰኘ ፕሮጀክት ሊተገበር ነው

120

 አዲስ አበባ ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ “ቤት ለሁሉም” የተሰኘ ፕሮጀክት ትግበራ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን የከተማዋ አስተዳደር ገለፀ። 

ከተማ አስተዳደሩ ለተቋማት ሕንጻ ኪራይ በየዓመቱ 650 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣም ተነግሯል።

ከሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ አዳማ ላይ የተካሄደው የአዲስ አበባ አስተዳደርና የክፍለ ከተሞች ዳይሬክተሮችና የቡድን መሪዎች ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በስልጠናው ማጠናቂያ ላይ ተገኝተው የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ከለውጡ በኋላ ከፍተኛ የአሰራር ማሻሻያ ከተደረገባቸውና ለውጥ ከመጣባቸው ዘርፎች መካከል የቤቶች ልማት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁንና ከከተማው የቤት ፍላጎት አኳያ የተሰራው ስራ ጎልቶ አለመውጣቱንና ግንባታው ፍላጎቱን ማሟላት ካልቻለ ቤት ተገንብቷል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።

ለ40/60 ቤቶች 100 ሺህ፣ ለ20/80 ደግሞ 600 ሺህ ያህል ዜጎች ተመዝገበው በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ነው ያነሱት።

ኢንጂነር ታከለ ኡማ በአዲስ አበባ አስተዳደር 125 ሺህ ቤቶች እየተገነቡ እንደሆነም ነው የገለጹት።

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለፃ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን ሁሉም የመዲናዋ ነዋሪ ቤት የሚያገኝበትን ሁኔታ የሚፈጥር ፕሮጀክት በቅርቡ ይፋ ይደረጋል።

ከባንክ ብድር ጋር ያሉ ችግሮችን በመፍታት የግሉን ዘርፍ በቤቶች ግንባታ ላይ በስፋት የማሳተፍ ስራ እንደሚሰራና አስተዳደሩ የቁጠባ ቤቶች ግንባታን ብቻ ለማከናወን ማቀዱንም አክለዋል።

በሌላ በኩል ከተማ አስተዳደሩ በስሩ ለሚገኙ ተቋማት የሕንጻ ኪራይ በየዓመቱ 650 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ ጠቁመው ይህን ማስቀረት የሚያስችሉ ተግባራትም እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ምክር ቤት 7ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባዔውን ትናንትናና ከትናንት በስቲያ ማካሄዱ ይታወሳል።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማም የ2012 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸምና የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ያካተተ ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም በከተማዋ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ተለይቶ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደሚዘጋጅላቸው ገልጸው ነበር።

እንደ እርሳቸው ገለጻም በተያዘው ክረምት መጨረሻ ድረስ የአርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ልየታ ስራ ይጠናቀቃል።

ከመሬት ጋር ተያይዘው ያሉ ብልሹ አሰራሮችን ማስቀረት የሚቻልበት ስርዓት መዘርጋት በበጀት ዓመቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ዋነኛው እንደሆነም ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።