በኦሮሚያ ክልል የተፈፀሙት ጥፋቶች የኦሮሞን ሕዝብ አይወክሉም

59

አዲስ አበባ ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ) የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀመው ጥፋት የኦሮሞን ሕዝብ እንደማይወክል የክልሉ መንግስት አስታወቀ። 

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በወቅታዊ ክልላዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳትና ውድመት መድረሱን አስታውሰዋል።

በክልሉ አጋጥሞ የነበረው ሁከት በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ /ሕወሓት/ አስተባባሪነትና በኦነግ ሸኔ ፈጻሚነት የደረሰ ጉዳት ነው ብለዋል።

የእነዚህ ሁለት የጥፋት ቡድኖች ዓላማ ሕዝቡን በብሔሩ፣ በኃይማኖቱና በማንነቱ እርስ በእርስ በማባላት አገር ማፍረስ እንደነበረም ጠቁመዋል።

አጥፊ ብሔርም፣ ኃይማኖትም የለውም ያሉት ኃላፊው የተፈጸመው ተግባር የኦሮሞን ሕዝብ አይወክልም ብለዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር አብሮ የሚኖርና አሁንም ለተጎጂዎቹ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ የክልሉ መንግስት በተፈጸመው የጥፋት ድርጊት የተሳተፉ አካላትን በመለየት ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝና ይህም ቀጣይነት እንዳለው አስታውቀዋል።

አያይዘውም በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የጥፋት ኃይሎች አሁንም የገበያና የትራንስፖርት አድማ ጠርተዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ለጥፋት ኃይሎች ጆሮውን ሳይሰጥ መደበኛ ሕይወቱን እየመራ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት ባለሀብቶች በነጻነት የኢንቨስትመንት ስራዎችን እንዲያካሄዱ ይፈልጋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የክልሉ ነዋሪዎች ኮቪድ-19ን እየተከላከሉ የክረምት ስራዎችን እንዲከውኑና የተጀመረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲያጠናክሩም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም