"የዛፍ አደሩ ኑዛዜ" 

168

"የዛፍ አደሩ ኑዛዜ"

(በአየለ ያረጋል)

እኔ ዛፍ-አደር ነኝ። አልዋሸሁም፤ እንቅጩን ነው የምጽፈው። የነብስዬን ጥሪ ነው የምጭረው። ተፈጥሯዊ ልቦናየን የምናገረው። ከመንፈሳዊ ልማዴ አንዱን የቀልቤን ማደሪያ ነው የምተነፍሰው። ከኢ-ንቁ አዕምሮዬ የተፈለቀቀ ሐቄን ነው የምናዘዘው። የእትብቴ ግብዓተ መሬት የተፈጸመበት ስፍራ ዛፍ ይበዛበታል። አገር በቀል ተክል፣ አካባቢ አደግ ዛፍ፣ ቀዬ አፈራሽ ዕፅ፣ መንደር አደር ቁጥቋጦ፣ ሰፈር በቀል ሳር… ሞልቷል። በርግጥ ገጠሬና ገበሬን፣ ጉብልና ተክልን ኑሮና ተፈጥሮ በግድም፣ በውድም ያዛምዳቸዋል። ለእኔ ግን ከዚህም ይልቃል። እኔና ዛፍ ፍቅር ነን። ለዛፍ እሳሳለሁ። ለዛፍ መሳሳቴን ባውቅም ለምን እንደምሳሳ ግን ልብ ብዬ አላቅም። (ዛፍ ወዳድነት በርግጥ ድንቅ እሴት ሳይሆን አልቀረም)። ለኑዛዜ ያበቃኝም ሰሞነኛ የአረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ ሙከራ ግን ዞር ብዬ ልብ እንድል አነሳሳኝ። ስለ ዛፍ አደርነቴ-መናዘዝ አማረኝ!!

የጮቄ ገመገም (ጎጃም-በቀድሞው ዳሞት አናት) አካል የሆነው የትውልድ ሰፈሬ ጫካ ሞልቷል። ልጅነቴን በስፍራው ከአያቶቼ ጋር ሳሳልፍ በግልገል የእረኝነት ዘመኔ ውሎዬ ከዛፍ ስር ነበር። ውርጩን፣ ተገቡን፣ ውሽንፍሩን፣ ቸፈቸፉን፣ ካፊያውን፣ አውሎ ነፋሱን፣ በረዶማ ዝናቡን የምናሳልፈው ከዛፎች ጉያ ተወሽቀን ነበር። ከማስታውሳቸው እጅግ ዕድሜ ጠገብ አገር በቀል ዛፎች መካከል ደግሞ ወይራ፣ አምቡስ፣ ዶንግ፣ ጥፌ፣ ገተም፣ አንፋር፣ ቆባ፣ ውልክፋ… ተጠቃሽ ናቸው። በቀየው ነዋሪ ከብት የሚሰማራበት ሜዳ (ኳኳቴ ይባላል) በግራና ቀኝ በጫካ የተከበበ ተዳፋታማ መልክዓ ምድር ኖሮት ሾጠጥ ያለ ከሰሜን ወደ ደቡብ የሚለጠጥ፣ አልፎ አልፎ ሞሶብ መሰል አምባዎች ያሉት ውብ መልክዓ ምድር ነው።

ከሜዳው በስተምስራቅ ካለው ጫካ ውሰጥ ደግሞ ከከፍተኛ ገደል የሚወረወር ፏፏቴ ያለው ለብር ወንዝ የሚገብር (ብር ወንዝ ከታላላቅ የአባይ ገባሮች አንዱ ነው) መኖሩ ደግሞ ይበልጥ ማራኪ ያደርገዋል። እናም ልጅነቴ በተፈጥሯዊ ጫካ (አንዳች ስንኳ እንግዳ ዛፍ ባልበቀለበት) የተዋበ ነው። የኛ ሰፈር ታዳጊ ቡረቃው፣ ድለቃው፣ ጨዋታው… ጫካ ውስጥ ነበር። አባሮሹ፣ እሩጫው፣ አላልይሆዩ… በዛፎች ዙሪያ ገባ ነው።

ከስድስት ዓመት በኋላ ቀዬ ቀየርኩ። ለፈጣን እግረኛ አንድ ሰዓት ወደ'ሚርቅ ቆላማ ሰፈር ወደ ወላጆቼ ተወሰድኩ። አባቴ ከከብቱ፣ ከአብሮ አደጉ፣ ከጫካው፣ ከአያቶቼ… ነጥሎ ሲወስደኝ አልቅሻለሁ። የወሰደኝም ጫካ ለጫካ ነበር (ጠፍቼ እንዳልመለስ ይመስላል)። በጉዞው ማልቀሴን ባለማቆሜም ከጫካው ዛፎች ‘ለበቅ’ እየቆረጠ ደብድቦኛል። አዲሱ አገርም ቢሆን በሰው ተከል ዛፍ የተሞሏ ነበር- ባሕር ዛፍ ተክል የተትረፈረፈበት። አንድ ቀን በዛፎች ውስጥ ለውስጥ ተሸሽጌ ከሰፈር ጠፋሁ።

መንገድ ላይ አንድ ዘመድ አግኝቼ  ቤታቸው ሰርግ ኖሮ ወሰደኝ። ለካስ አባቴ ቀድሞኝ ሰርግ ቤት መጥቶ ኖሮ አያቶቼ ቤት ሳልደርስ መልሶ ይዞኝ መጣ። ሲያመጣኝ ግን ዛፍ ስር እያሳረፈ እየደበደበ ነበር። የጠላሁትን የወላጆቼን ቤት በግድ ለመድኩት። ከሰፈሩ ልጆች ጋር ተላምጀ በተለይ በአካባቢው ከነበረ የሸንበቆ ጫካ ውስጥ ጨዋታ ጀመርኩ። (በሕይወቴ በልዩ ሁኔታ ከምወዳቸው ዕፅዋት መካከል ሸንበቆ ዋነኛ ነው። ዛሬም በአዲስ አበባ በርካታ ሰፈሮች ሳዬው በናፍቆት እመለከተዋለሁ)። ዛፍ ላይ መንጠላጠል ለመድኩ። ከሰፈሩ የሰው ጦጣዎች መካከል አንዱ ሆንኩ።

ልክ በመጀመሪያ ቀን ትምህርት ቤት የገባሁ ዕለት ማታ የተደበደብኩትም ከትምህር ቤቱ ፅድ ዛፎች ላይ ስንጯለል አንድ ብር የተገዛ “ቢክ” እስክብሪቶ በመጣሌ ነበር። ዛፍ የመንጠላጠል ልምዴ ትምህርት ቤታችን ሰንደቅ ዓላማው ከማክበሪያ (መስቀያ ላላማለት ነው) ብረቱ ጫፍ ላይ ተሰንቅሮ ለማውረድ ሲያስቸግር ሰንደቁን ብረቱ ላይ ተንጠላጥሎ ለማውረድ ከሚጣሉ (እኔ ላውርድ እኔ ላውርድ) ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ እንድሆን አስችሎኛል)።

የገጠር ልጅ ተማሪም፤ ገበሬም ነው። የከብት እረኝነትም፣ ገበሬ ቤተሰብን ማገዝ ያው የግብርና አካል ነውና። ትምህርት ቤቴ ከአንድ ሰዓት በላይ ይርቃል። በ1967 ዓ.ም በስዊዲን መንግስት እርዳታ የተሰራው ትምህርት ቤቴም በሚያማምሩ ፅዶችና ባህር ዛፎች የተዋበ ነው። የትምህርት ቤቱ ርቀት እጅግ አድካሚ ነው።

የጥቢና የግቢ ወራት ብርድ፣ ዝናብና ቅዝቃዜ፣ የሐጋይ ወራት ሐሩርና ጸሐይ አይጣል ነው። እናም እኛ የአስከሏ ተማሪዎች ዝናብ ሲዘንብም፣ ፀሐዩ ሲበረታም መጠለያችን ዋሻ አይደለም- በየመንገዱ በሚገኝ ዛፍ እንጂ። ውሃ ሲጠማንም የምክንጠጣውም በዛፎች በተከበቡ ምንጮች በመፈለግ ብቻ ነበር። ርሐብም ሲኖር ዛፎች ላይ ተንጠላጥሎ ፍራፍሬ መልቀም የተለመደ ነበር። በተለይ ዶቅማ፣ ቀጋ፣ ሾላ፣ አሽቃሞ፣ ኮርሽምና እንጆሪ በብዛት ለምግብነት የሚውሉ ዛፎች ነበሩ።

ከትምህርት ቤት መልስ ወይም ትምህርት በሌለ ቀንም እረኝነቱ (ከብት ማገዱ) ከዛፎች አይለይም። ተረኛ ከብት ጠባቂ ከሆንኩ በዛፍ በተሞላው ተረተር (ተራራማ ሜዳ) እውላለሁ። ካልሆንኩም በስፍራው ከቀየው ልጆች ጋር እውላለሁ። የራሴን ከብቶች ነጥዬም ዛፍ ባልተለየው መንደር አግዳለሁ። የምሳ ዕቃ፣ ገሳው ወይም ሌላ መገልገያ የምናስቀምጠቅውም ዛፍ ላይ ነው። ለከብቶች ማገጃ ሽመልም ከዛፍ ነው። አንዳንዴም ሳር በጠፋ ጊዜ ከዛፍ ቅጠሎች ቆርጨ ከብቶቼን እመግባለሁ።

ዛፍ ለኛ ሰፈር ገበሬ ሁሉም ነገሩ ነው። መኖሪያ ቤቱ እንጨት ከዛፍ ነው። ቆጡን የሚሰራው ከዛፍ እንጨት ነው። እርፉ፣ ቀንበሩ፣ ሞፈሩ፣ ድግሩ፣ ቅንጭርቱ እንዲሁም የጅራፍ፣ የምሳሩ፣ የማጭዱ… የሌላም መገልገያ መሳሪያው እጀታ ከዛፍ ነው።  የምርቱ መውቂያው፣ የምርቱ ማጣሪያ መንሹና ላሜዳው ከዛፍ ይዘጋጃል። ማሳ ላይ እህል ውሃ (ምሳ) የሚያስቀምጠው ዛፍ ስር ነው።

በሬውን ከእርሻ ፈቶ ሞፈርና ቀምበሩነም የሚያስቀምጥ ዛፍ ላይ ነው። ኮብላይ የንብ መንጋ ለማጥመድ ቀፎውን የሚሰቅለው ከዛፍ ላይ ነው። አውድማ ጥሎ ምርቱ በአንድ ቀን ወደ ቤት ካልገባም የገበሬው አዳር ዛፍ ስር ነው። ገበሬው ስራ ውሎ የሚሞቀው እንጨት የዛፍ ውጤት ነው። ገበሬዋ ምግብ የምታበስለብት ማገዶ የዛፍ አካል ነው።

ከዛፍ ጋር እኔን ያስተሳሰሩኝ ገጠመኞች በርካታ ቢሆኑም አንዷን ላንሳ። ይህም ለዚህ ጽሁፍ ርዕስ የመረጥኳት ‘ዛፍ አዳርነቴን’ የምታረጋግጥ አንድ ገጠመኝ አለች። መስከረም ጥባት ወይም ንሐሴ መጨረሻ አካባቢ ይመስለኛል። ወቅቱ ዝናባማ ነበር-እንደሰሞኑ ነዝናዛ ቀናት። በአንድ አመሻሽ ከሰፈር ልጆች ጋር ዋዛ ስንቀዳ (ስንጨዎት) የኔ ከብቶች ተነጥለው ከሰው አዝመራ (የጤፍ ሰብል ይመስለኛል) ገቡና ባለአዝመራው ሰው በቀጥታ ለቤተሰብ ስሞታ (አቤቱታ) በመናገሩ ቤት መሄድ ፈራሁ (የተደባዳቢ አባቴን በትር)። ከብቶችም ቤት ሄደው እኔ ሜዳ ቀረሁ።

ጎረቤቱ ሁሉ ቢፈልገኝ ተሰወርኩ። የዘመድ አዝማድ ቤት ሁሉ ተጠየቀ። ምሽቱ ተጋመሰ። ፈላጊ ቤተሰብና ጎረቤት ተስፋ ቆርጦ ወደ ቤት ተከተተ። ያ ሁሉ ሲሆን እኔ መጀመሪያ አንድ ቁጥቋጦ ውስጥ ተደብቄ ከቆየሁ በኋላ ቀኑ ሲጨልም ግን ከቤታችን 500 ሜትር ከሚገመት ርቀት ላይ ከነበረ ትልቅ ባሕር ዛፍ ላይ ነበርኩ። ከፍተኛ ዝናብ ነበር ቻልኩት። ሲበርደኝ ከዛፍ ወርጄ ከቤታችን በረንዳ ለመጠጋት ስሞክር የሌሊት አራዊት (ጃርት) በዛፉ ስር ሲያልፉ አይቼ ፈራሁ።

ቁልቁል ስመለከት ከወጣሁበት ዛፍ ስር መሬት ላይ ደግሞ ጅብ የመሰለ ነገር ተኝቶ ያየሁ መስሎኝ በፍርሃት እራድኩ (ጥዋት ሳየው በርግጥ ትልቅ ግንድ እንጂ ጅብ አልነበረም)። ከቤታችን የነበሩ ሁለት ሃይለኛ ውሾች (በእብድ ውሻ በሽታ ተለክፈው ከመሞታቸው በፊት) አጠባብ ላይ ሲጮሁ አባቴ ከቤት ወጥቶ በጓሮ ሲፈልገኝ አስተዋልኩ። በመቀጠልም ጥንድ ውሾቹን አስከትሎ ከወጣሁበት ባሕር ዛፍ ስር (መንገድ ዳር ስለነበር) አልፎ ሲሄድ ተመለከትኩ (ጥዋት ወደ አያቶቼ አገር እንዳልሄድ ቀድሞ ለመጠበቅ ይመስላል)። መቼስ አይነጋም የለም ነጋ፣ ብርድና ቅዝቃዜውን ችዬ የዛፍ ቅርንጫፍ ተቸብቤ ነጋ። ጥዋት ከዛፍ ወርጄ በአቅራቢያ በነበረ ወንዝ ገብቼ በዛፍ ስር ተሸሸኩ። በጣም ርቦኝ ስለነበር ረፋድ ላይ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኝ የቦቆሎ ማሳ አገዳ ለመብላት (ቦቆሎ መጋጥም ይቻላል) በማሰብ በሰብሎች መሃል እየተሹለከለኩ መጓዝ ጀመርኩ። ግን ከተራራ ሆነው ያዩኝ የሰፈር ልጆች ‘ስሜን እየጠሩ’ ተጯጯሁ (የመጥፋቴ ዜና በሰፈር ተናኝቶ ነበርና)። አባቴም በርቀት ተጣርቶ ከቆምኩበት ስፍራ እንድጠብቀው ነገረኝ። ሩጨ አላመልጥ፣ የምሄድበትም አላቅ ነገር በፍርሃት ጠበኩት። ግን የልብሴን መከርሰስ አይቶ አዘነ (አውሬ ይበላዋል ብሎም ሰግቶ ኖሯልና አልተቆጣም)።

ቤት ወስዶኝ ምግብ ከበላሁ በኋላ እንደተለመደው ወደ ከብት ማሰማሪያ ሜዳ ተላኩ። ከዛ በኋላ ዛፍ ላይ የማደሬ ዜና በመንደሩ ከተሰማ በኋላ ድፍረቴ ተደነቀ፤ እንቅልፍ የሌለው ጀግና ተባልኩ። በሰፈራችን የመጀመሪያውም፣ የመጨረሻውም ‘ዛፍ አደር’ እኔ ሳልሆን አልቀርም።

ግን የዛፍ ገጠመኜ ስላለኝ አይደለም፤ በተፈጥሮዬ ዛፍ እወዳለሁ። ዛፍ የሚገኘው ደግሞ ተተክሎ ነው። እናም ዛፍ መትከል ከልጅነቴ ጀምሮ የምከውነው ልማዴ ነበር። አባቴ ችግኝ ተክሎ አይጸድቅለትም ነበርና እኔን ያስተክልም ነበር። አንድ ዋንዛ ብቻ ጸድቃለታች። እሷም በቅዳሜ ቀን የተከላት ስለነበረች ‘በባል (ከስራ ቀናት ውጭ) ስለተከልኳት ነው’ በማለት ሁሌ ሲፀፀት እሰማው ነበር (በሰንበት ወይም በበዓላት ቀን  ዛፍ መትከል ቀርቶ በሰንበት የተቀዳ ውሃ እንኳን በጎጃም እንደ አስኮናኝ ድርጊት ይቆጠራል)። እኔ ግን ‘እጀ-ለምለም’ የምባል ልጅ ነበርኩ።

ባዶ ማሳ ላይ የሰራነው ቤት ነበርና ዙሪያውን በገመሮ፣ ስሚዛ (ሰንሰል) እና በግራዋ እንዲሸፈን አደረኩ። መትከል ብቻ ሳይሆን እንከባከባለሁ፤ ሲቆረጡም እበሳጫለሁ። ለምሳሌ፤ ከቤታችን አቅራቢያ ከነበረ አማጋ (የወል መሬት) ግማሽ ሜትር የምትሆን መሬት ቆፈሬ፣ የባህር ዛፍ ዘር አምጥቼ አፈላሁ (አበቀልኩ)። በሰፈራችን የነበረ አንድ ምቀኛ ሰው አንድ ቀን በስፍራው በመጣ የቀበሌ ሊቀመንበር አመልክቶ ሊቀመንበሩ በለበሰው ቦት ጫማ ረከረከብኝ (ቦታው የወል ሜዳ ስልሆነ ለምን አጠርክ በሚል)። ይሄኔ ክፉኛ አልቅሻለሁ። የተራረፉትን የባሕር ዛፍ ቡቃያዎች ግን ተንከባክቤ አሳደኩ። (ከዓመታት በኋላ በስፍራው ትምህርት ቤት ተገንብቶ ስለነበር የመምህራን ቤት ከፊት ለፊቱ በመሆኑ የእኔ ባህር ዛፎች እንደ ጥላ ያገለግሉ ነበር፤ በቅርብ ዓመት በፊት ተሽጠው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ሰምቻለሁ)።

በተመሳሳይ ከጓሯችን የተከልኳት ባሕር ዛፍ ካደገች (ለአቅመ ዛፍ ከደረሰች) በኋላ አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ስመለስ በቤታችን በነበረ ድግስ ማገዶነት ወደ ፍልጥነት ተለውጣ ባገኘሁ ጊዜ ክፉኛ ተከፍቻለሁ። ቁልቋል ዕድሜ ያረዝማል ሲባል ሰምቼም ብዙ ቍልቋል ተክዬ አሳድጊያለሁ። ደን አካባቢ ስሄድ ልዩ ልዩ አበባ ያላቸው ዕጽዋትን ፍሬ እሰበስብ ነበር። ከነዚህም መካከል ‘ሰርክ አዲስ’ የተሰኘ የሚያምር አበባ ያለው ተክል በደጃችን ተክየ አሳድጊያለሁ። ትምህርት ቤታችን (እስከ 8ኛ ክፍል ከተማርኩበት) ከጓደኞቼ ጋር ሆነን በየዓመቱ ትምህርት ቤቱ ከሚያደርገው የዛፍ ተከላ ዘመቻ ባሻገር በትምህርት ክፍላችን ፊት ለፊት ባህር ዛፍ አሳድገናል።

የዕፅዋት ዘር መሰብሰብ እወድ ነበርና በ2000 ዓ.ም (7ኛ ከፍል እያለሁ) ከጎጃም ወደ ወለጋ ጠፍቼ ለሁለት ወራት ቆይቼ ስመለስ ዝግባ፣ ባጉራ፣ ብርብራ፣ … ሌሎች ስማቸውን የረሳኋቸው ታላላቅ አገር በቀል የዛፍ ዘሮች ሰብስቤ ወደ ጎጃም ለመውሰድ (አባይን ለማሻገር መሆኑ ነው) አቅጄ ነበር-በአጋጣሚ በግል ችግር ሳልችል ቀረሁ እንጂ። ሃሳቤ ባለመሳካቱም ሁሌ ይቆጨኝ ነበር። እኔ "ዛፍ አደሩ" ደን ሲጨፈጨፍና ሲቃጠል እቆረቆራለሁ። 6ኛ ክፍል እያለሁ በአካባቢያችን ቋያ እሳት ተነስቶ አስማ የሚባለውን ተራራ አቃጠለው። እኔም ‘አስማ ተራራ በመቃጠሉ በርካታ ዕጽዋት ወደሙ፤ በርካታ ቆቅና ጅግራዎች በረሩ፤ ሚዳቋዎችን ወደ ጎረቤት ቀበሌዎች ተሰደዋል’ የሚል ዜና ሰርቼ ትምህርት ቤታችን ሰልፍ ላይ በሕይወቴ የመጀመሪያ ዜና አቅርቤ ነበር። በዚሁም ከመድረክ ሳልወርድ በትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር (ጋሽ አወቀ) ሁለት ደብተሮች ተሸልሜያለሁ (ለተፈጥሮ ስነ ምህዳር መቆርቆር የጀመርኩት ተማሪ ሳልሆን አልቀርም…ሃሃሃ…)።

አባቴ ከ1997 በኋላ ወደ ወደ ጎንደር ምዕራብ አርማጭሆ ስራውን ስላዞረ (የሰሊጥ ገበሬ ስለሆነ) እኔ ደግሞ ከ2001 ዓ.ም ጀምሬ (ወደ 9ኛ ክፍል ስዛወር) ለክረምት ወራት እሱ ጋር እመላለስ ነበር። በመጀመሪያ ጊዜ የዕፅዋትና የከተማ ውበት በእዕምሮዬ የተቀረጸው ጎንደር ከተማ አክሱም ሆቴል በዛፎች ስር የተኮለኮሉ አምፖሎች የኮረንቲ ድምቀት ነበር። በዕፅዋት ቅጠል ውስጥ ብርሐን ሲፈነጥቅ የሚፈጥረው ውብ ፀዳል። በመስከረም ወደ ትምህርትን ቤት ስመለስ በአክስቴ መኖሪያ ግቢ (ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩበት ቤት) በግቢው ዛፎች ቅጠላ-ቅጠሎች መሃል የመብራት አምፖሎችን በመትከል ያየሁትን አድርጊያለሁ። አርማጭሆ ቆይታዬ የበርሐ ዛፍ (ሚሚ ይባላል) በደጃፋችን በመትከል አሻራዬን አስቀምጫለሁ፤ አሻራዬም ፍሬ ማፍራቱን አረጋግጫለሁ። ወደ ዩኒቨርሲቲ (አዲስ አበባ) በገባሁ ጊዜ ከታሪካዊ ቤቶች በተጨማሪ ቀልቤ የሚያርፈው በከተማው ውስጥ ስላሉት አገር በቀል ዛፎች ነው።

በመንገድ፣ በህንጻ ግንባታ በርካታ ትውልድ ያስቆጠሩ ዛፎች ሲቆረጡ ከውስጤ ይከፋኛል። የጋዜጠነትና ተግባቦት ትምህርት ቤታችን (የቀድሞው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ግቢ) ለህንጻ ግንባታ ሲፈርስ ከታሪካዊ ህንጻዎች ባሻገር በግቢው የነበሩ እድሜ ጠገብ ወይራ ዛፎች መውደም ዛሬም ይከነክነኛል። በኛ ትውልድ ተክለናቸው የማይደርሱ እድሜ ጠገብ ዛፎች በኛ እጅ ሲወድሙ ያሳዝናል።

የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ለአማርኛ መምህራችን የሕይወት ታሪክ ሳነብ የጠቀስኩት የወደፊት ሕልሜን ‘ጋዜጠኛ’ ሆኖ ከአገር አገር መዞር ወይም ‘ደራሲ’ መሆን የሚል ነበርና ምናልባት አንዱን ሙያ ሳልጀምረው አልቀረሁም። እናም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኘ ከዛም በኋላ በስራ አጋጠሚ (በጋዜጠኝነት) በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ስዞር ከሁሉ በላይ የማጤነው መልክዓ ምድርና ስነ ምህዳር ይመስለኛል። በሕይወቴ ምናልባትም የዕጽዋትን ያህል በሞባይል ካሜራ ያስቀረሁት ነገር ያለ አይመስለኝም። በርካቶቹም በዚህ ድርጊቴ (የዛፍ ፍቅር) ይሳለቁብኛል። ‘ይህን ዛፍ ታውቀዋለህ?’ ከተማ ውስጥ ሳይቀር በቅንነት ለወዳጆቼ የማቀርበው ጥያቄ ነው። በርካቶቹ ግን እንደ ቂል የሚቆጥሩኝ ይመስለኛል። ምዕራብ ሐረርጌ፣ የሻሸመኔ-ኮፈሌ (ምዕራብ አርሲ)፣ የነቀምቴ-መቱ (ወለጋና ኢሊባቦር)… መስመሮች በተፈጥሮ ዕፅዋት ሐሴት ያደረኩባቸው ስፍራዎች መካከል ናቸው። አካባቢዎችን ሳስታውስም ያስተዋልኳቸው ዕፅዋትን አልዘነጋም።

በአብያተ ክርስቲያነት ዋርካ ዛፎችን በአዕምሮዬ ተስለዋል። አክሱም ሐውልትን ልብ ስል ከሐውልቱ ግርጌ ከጽዮን ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ግርጌ ያለችዋን ዋንዛ፣ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያትን ሳስታውስ ከቤተ ጊዮርጊስ በቀኝ ራስጌ ያለችዋ ወይራ ዛፍ፣ የጎንደር አብያተ መንግስታትን ሳሰብ ጃን ተከል ዋርካ፣ ስለባሕር ዳር ስሰማ ዘንባባዎቿ… በአይነ ህሊናየ ይከሰታሉ።

እንደማጠቃለያ በአንዳንድ ነጥቦች ልሰናበት። አንዳንድ ዛፎች መቸስ ግሩም ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከአብይ አህመድ በፊት ከነበሩ መሪዎች ለዛፍ ልዩ ፍቅር የነበራቸው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ይመስሉኛል። ዛሬ ከአንድ ክፍለ ዘመን ከሩብ በላይ (ከ130 ዓመት በላይ) ዕድሜ ያላቸው ዛፎችን በዘመናቸው በየቦታው ዛፍ ይተክሉ ነበር። (ያኔ ምኒልክ ጉድጓድ አስቆፍረው የተከሏቸው ችግኞችና ዛሬ ግን እድሜ ጠገብ ዛፍ የሆኑ)።  እኔ እንኳን ሶስት ቦታ ዛፎቻቸውን አይቻለሁ።

እነሱም እንጦጦ ከአውስትራሊያ ያስመጡት ባሕር ዛፍ፣ በትውልድ ቀያቸው አንጎለላ የተከሉት የ’ሾላና የኮርች’ ዛፍ እንዲሁም ወሎ ውስጥ በመሰረቷት የወረ-ኢሊ ከተማ የሚገኘው ‘አባ ግንባሩ’ የተሰኘው የጽድ ዛፎ ናቸው።  ምኒልክ ዛሬ ለኢትዮጵያዊያን የጀርባ አጥንት የሆነውን ባሕር ዛፍ (የባሕር ማዶ ተክል) ከአውስትራሊያ ሲያስመጡ እንጦጦ የነበረው ቤተ መንግስታቸው አካባቢ በመራቆቱና ቤተ መንግስታቸውን ወደ አዲስ ዓለም ለመዛወር ስራ ላይ እንቅስቃሴ ላይ እያሉ ‘ኢኩሊፕተስ’ የሚባል በፍጥነት ለማገዶ የሚደረስ ዕጽ እንዳለ ከአንድ ፈረንጅ ተነገራቸው።

ሰምተው ግን በግብታዊነት ሳይሆን ሌሎች የውጭ አገር ዜጎችን ጠይቀው የዛፉን ውጤታማነት በማረጋገጥ ፍሬውን አስጥተው ተከሉ። ሕዝባቸው የባሕር ዛፍ እንዲተክልና ውጤታማ ስራ ለማከናወን ግን አንድ የችግኝ ፖሊሲ አወጁ። እሱም ባሕር ዛፍ የሚተክል ባለመሬት ‘ግብር ምሬዋለሁ’ የሚል ነበር። አገሬውም ለግብሩ ሲል የባህር ዛፍ ችግኝ መትከሉንና በኢትዮጵያ የባህር ዛፍ ነገር መስፋፋቱን ጳውሎስ ኞኞ ይተርክልናል። ሌላው በአያታቸው በጥንታዊቷ የንጉስ ሣህለሥላሴ ቤተ መንግስት ባድማ በአንጎለላ የሚገኘውን ኮረች ዛፍ ምኒልክ የተከሉት ለመብረቅ መከላከያነት በማሰብ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል(ተፈጥሯዊ ችግርን በተፈጥሯዊ መፈትሄ መስጠት)።

በነገራችን ላይ ከሳምንት በፊት በስፍራው ለስራ ተገኝቼ በታሪካዊ ስፍራ ታሪካዊ አረንጓዴ አሻራ አሳርፊያለሁ። ቀደም ባሉት ወራት በስፍራው ያገኘሁት የአካባበው ነዋሪ በልጅነቱ ከአንድ ጓደኛው ጋር ሾላው ላይ ወጥተው ደብረ ብርሃንን ከተማን ለማየት (10 ኪሎ ሜትር ይርቃል) ዛፉ ላይ ሲንጠላጠሉ ጓድኛው ከምኒልክ ዛፉ ወድቆ አካሉ ለስብራት መጋለጡን አጫውቶኛል። ለስብራት የተጋለጠው ጓደኛው ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ ጤና ተቋም ሜዲካል ዶክተር እንደሆነ አጫውቶኛል-ይህም አስገራሚ ታሪክ ነበር።

በርግጥ ዕጽዋት ለሕይወታዊያን ሁሉ የሕልውና መሰረት ነው። ችግኝ መትከል ፖለቲካ የሚመስላቸው (የሚያደርጉትም) በርካታ ናቸው። የምኒልክ ችግኝ ለራሳቸው ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ መሰረት እንጂ ለዘመናቸው ፖለቲካ አላገለገለም። ባደኩበት አካባቢ ግንቦት 20 በዓል በደርግ ዘመን በለማ ዛፍ ውስጥ ነበር የሚከበረው። ከ80 በመቶው በላይ ህዝቧ ገበሬ በሆነባት ኢትዮጵያ የደን ልማት ምን ያሀል የሕልውና ጉዳይ እንደሆነ ልብ ማለት ያሻል። በአንድ ወቅት ዶክተር መኩሪያ አርጋው (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው) ለዜና ግብዓት በሰጡኝ ቃለመጠይቅ ‘ዕጽዋትን ለመጠበቅ ‘የተፈጥሮ እረኝነት’ ያስፈልጋል ብለውኝ ነበር። የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ሥራዎች ማለትም ስነ ሕይዋት፣ አፈርና ውኃ ተያያዥ ሀብቶች ስለሆኑ ለሶስቱም እረኝነት ያስፈልጋል ነበር ያሉኝ። ድርቅን ለመቋቋም የተፈጥሮ ሚዛንን መጠበቅ (የደን፣ አፈርና ውህ መስተጋብሮች) ግድ ይላል።

ዶክተር መኩሪያ ሲያብራሩም ደን ከሌለ ዝናቡ አፈር ውስጥ አይሰርግም ወይም ከርሰ ምድር ውሃ ይጠፋል፤ ከርሰ ምድር ውሃ (የአፈር እርጥበት) ከሌለ ደግሞ በስነ ሕይወት ሕግ መሰረት ዕጽዋት ምግብ የሚሰሩት ከውሃና ከአየር ነውና ደን አይኖርም። ይህ ደግሞ ድርቅን ያመጣል። ድርቅ ደግሞ ርሃብን፣ ርሃብም ሞትን እየጠራ የሰው ልጅ ሕልውና ይፈተናል። መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮችም (እንደ መፍትሔ) አንኳር አንኳር ነጥቦችን ጠቅሰውልኝ ነበር። የመጀመሪያው ከአራት ትውልድ በላይ የሚያገለግል ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቅም ፖሊሲ ያሻል፤ የመሬት አጠቃቅም (የአፈርና ውሃ እቀባ) ህግና መመሪያዎች ገቢራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።

የሰብል አመራርት ዘዴን በመቀየር (ለምሳሌ መስኖ ልማት በመጠቀም) የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንጂ ደን እያወደሙ እርሻን ማስፋፋት ተገቢ አይደለም። የተቀናጀ ስነ አካላዊና ስነ ሕወታዊ ስራዎችን መተግበር፣ ለእርሻ የማይውል ተዳፋታማ መሬቶችን በደን ልማት ማዋል እንደሚገባም ይመክራሉ። ውሃን ከመነሻው እስከ መደረሻው ያቀፈ የተፋስስ ስራዎችን (ለምሳሌ አባይ፣ አዋሽ፣ ተከዜ) ማከናወንም ይገባል። አርሶ አደሩ በተበጣጠሰ መሬት ድንበርና በመንገዶች ዳርቻዎች አካባቢ ዛፍ መትከል እንዲሁም ለእርሻ የማይሆኑ ፉካ (የተጋጋጡ ተራራዎችን) መሬቶችን በደን እንዲያለሙ ለወጣቶችና ባለሃብቶች ማበረታቻዎችን በመስጠት (የዳግማዊ ምኒልክ ግብር ቅነሳ ምሳሌ ሊሆን ይችላል) የዴን ሽፋንን ማሳደግ ይቻላል ባይ ናቸው።

ከእንጨት ውጤቶች ፋብሪካዎች ጋር አስተሳስረው እንዲያለሙ ቢደረግ የ10 ወይም የ20 ዓመት እድሜ ስራ እንደሆነ ይገልጻሉ። ፉካ (ምድረ በዳ ተራሮች) መሬቶችን በዴን በመሸፈን በ10 ዓመት ውስጥ የኢኮኖሚ ምንጭ ማድረግ እንደሚቻል በቻይና (አገረ ፈረንሳይን አራት እጥፍ የሚያህል ስፋት ያለው መሬት) በፍራፍሬ በመቀየር በተግባር ተረጋግጧልም ይላሉ ዶክተር መኩሪያ።

እናም የኢትዮጵያ ተራሮችን ለዘላቂ ልማት ይዋሉ፣ ተፋሰሶች ይጠበቁ፣ ለዚህም ፖሊሲ ተቀርጾ ገቢራዊ ይደረግ። ሰዎችና እንስሳት ለዕፅዋት አደር (ግፋ ቢል ዛፍ-አደር) ስለሆን ለዕፅዋት ልብ ማለት ይገባናል። አረንጓዴ አሻራችን ለኛም ሆነ ለቀጣይ ትውልዶች ትንፋሽ ነው። ካልተነፈሱ ደግሞ እንዴት ይኖራል? አረንጓዴ አሻራችሁን አትሙ። እንደኔ የዛፍ ፍቅር ይስጣችሁ!!

ከሰላምታ ጋር

                                                                                                               ከዛፍ አደሩ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም