የአዲስ ከተማ ተወላጆች ለአቅመ ደካሞች ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

49

አዲስ አበባ ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ) በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የአዲስ ከተማ አካባቢ ተወላጆች  ከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ  ለችግረኛ ቤተሰቦች ድጋፍ አድርገዋል፡፡

 ለአረጋውያኑ እና ለአቅመ ደካች  ከተደረጉት የምግብና የንጽህና መስጫ ቁሶች መካከል ሩዝ፣ዱቄት፣ ዘይት፣ ሳሙና እና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች ይገኙበታል፡፡

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማህበራዊ ትረስት ፈንድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፍቅርተ ነጋሽ "በድጋፉ የተሳተፉ የአዲስ ከተማ ተወላጆች  የወገን አለኝታነት ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።

 ወይዘሮ ፍቅርተ ነጋሽ በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ የአዲስ ከተማ ተወላጆች ከፈጸሙት ተግባር ሌሎች ትምህርት በመውሰድ ለወገኖቻቸው የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 ሕብረተሰቡ ራሱን ከኮሮናቫይረስ በመጠበቅ በኩል የሚያሳየው መዘናጋት ከቀን ቀን እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ፍቅርተ፣ "ሁሉም ዜጋ ወረርሽኙን ለመከላከል የወጡ የጥንቃቄ መመሪያዎችን በሚገባ ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል" ብለዋል፡፡

 የአዲስ ከተማ በጎ ሥራ መረዳጃ ስብስብ ሰብሳቢ አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በርካታ ዜጎች ለችግር መጋለጣቸውን  ጠቁሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለውን በማካፈል የወገን አለኝታነቱን እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርቧል።

 በዛሬው ዕለት ድጋፍ የተደረገላቸው  ነዋሪዎች  ድጋፍ ላደረጉላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበው በፈረሱ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ አቅመ ደካማ ወገኖች ትኩረት እንዲያገኙም ጠይቀዋል፡፡

 "ይህ ጊዜም ያልፋል፤ ህይወትም ይቀጥላል" በሚል   መሪ ቃል በተዘጋጀው   መርሀግብር   የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች እና ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም