የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ100 ቀናት ዲፕሎማሲ

83
ምህረት አንዱዓለም /ኢዜአ/ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፥ ባለፉት 100 ቀናት ወደ ውጭ ሀገራት በመሄድ፣ መሪዎችን በመቀበልና በስልክ ውይይት በርካታ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ሰርተዋል። በተሾሙ በ97ኛው ቀን ኢትዮጵያና ኤርትራ ከጠላትነት ወጥተው አዲስ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት የተፈራረሙበት የዲፕሎማሲ ስኬትም ይጠቀሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከተሾሙ እነሆ 100 ቀን ሆኗቸዋል። ዶክተር አቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መጋቢት 24/2010 ዓ.ም ሲሾሙ ንግግር አድርገው ነበር። በዚህ ታሪካዊ ነው በተባለ ንግግራቸው ምስራቅ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት በቀውስና በተለያዩ ኃይሎች ፍላጎት ሥር የወደቀ ቀጠና መሆኑን አንስተዋል። ቀጠናው ወስብስብና መጠላለፍ ያለበት በአንጻሩ ደግሞ በባህል በቋንቋና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰረ ሕዝብ የሚኖሩበት አከባቢ መሆኑንም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን አጠናክራ እንደምትቀጥልና  ከአፍሪካውያን ጋር በችግርም በተድላም አብራ እንደምትቆም በዕለቱ በአፅንኦት መናገራቸው የሚታወስ ነው። ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃ ከልብ እንፈልጋለን፤ የበኩላችንን እንወጣለንም ብለው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት 100 ቀናት በመጀመሪያ ቀን የምክር ቤት ንግግራቸውን ከሀገር ውስጥ ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ በተግባር አሳይተዋል። ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ከማስፈታት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር አዲስ ወዳጅነት እንድትጀምር እስከማድረግ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ስርተዋል። ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ100 የሹመት ቀናቸው ውስጥ እነማን ሀገራትን ጎበኙ፣ ከማን ጋር ምን ለመስራት ተስማሙ የሚለውን እንመልከት። ከተሾሙ አንድ ወር ሳይሞላቸው እረፍት አልባ የሆኑት ዶክተር ዐቢይ የመጀመሪያ የምስራቅ አፍሪካ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን ወደ ጂቡቲ አድርገዋል። የለውጥ መሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉብኝታቸው ወቅት ለኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ወሳኝ በር የሆነውን የጅቡቲ ወደብን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። ኢትዮጵያ የጅቡቲን ወደብ በጋራ ለማልማትና የንግድ ባለድርሻ እንድትሆን የሚያስችላቸውን ስምምነት ከፕሬዚዳንት ኦማር ጌሌ ጋር ፈጽመዋል። በተመሳሳይ የሀገራቱን ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለመፍጠር የጅቡቲ መንግስትም ከኢትዮጵያ ትላልቅ የመንግስት ተቋማት ላይ ድርሻ ወስዶ እንዲሰራም ጥሪ ቀርቦለታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የምስራቅ አፍርካ ጉዟቸውን ቀጥለዋል፤ በተሾሙ በአንድ ወራቸው ቀጣይ የቀጣናው መዳረሻ ያደረጓት ሀገር ደግሞ ሱዳንን ነው። ካርቱም ላይ ከፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ጋር የተገናኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ከማስፈታት እስከ ዓባይ ጉዳይ የዘለቀ ውይይት እና ስምምነት ነበራቸው። በዚህም የሱዳን መንግስት በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ 1 ሺህ 400 ኢትዮጵያዊያንን ከእስር ፈትቷል። በኢትዮጵያና በሱዳን ያለው ስትራቴጂክ አጋርት እንዲቀጥል ለቀጣናውም ሆነ ለአፍሪካ ሰላምና ብልጽግና በጋራ ለመሥራት መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን ዶክተር ዐቢይ ለሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር አንጸባርቀዋል። በዓባይ ጉዳይ ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ለያዘችው አቋም አመስግነው፤ ይህም ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ የቀረበውን ከፊል የሱዳን ወደብ በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ተስማምተው ነው የተመለሱት። ዶክተር ዐቢይ ወደ ኬንያም አቅንተው ነበር፤ በዚህ ጉብኝታቸው ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ከማስፈታት ጀምሮ ኢትዮጵያና ኬንያ ለረጅም ዘመን የዘለቀውን ታሪካዊ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ ከፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተስማመተዋል። ሞያሌን የምስራቅ አፍሪካ የምጣኔ ኃብት እምብርት ለማድረግም በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ላይ ደርሰዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኬንያ አየር መንገድ በትብብር እንዲሰሩ፤ እንዲሁም የላሙ ወደብን በጋራ ለማልማት መስማማታቸው በውቅቱ ይፋ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ እረፍት የለሽ የዲፕሎማሲ ጉዟቸውን አላቆሙም። በፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ግብዣ መሰረት ወደ ኡጋንዳ አቅንተው ሁለቱ ሀገራት በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ከሙሴቬኒ ጋር የተስማሙ ሲሆን የኡጋንዳን ከፍተኛ ሜዳሊያ ተሸልመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኡጋንዳ በቀጥታ ወደ ግብፅ ነው ያመሩት፤ በካይሮ ጉብኝታቸው ከፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ጋር ባደረጉት ውይይት 32 ኢትዮጵያውያን እስረኞችን አስፈትተው ወደ ሀገራቸው ይዘው ተመልሰዋል። ሊቢያ ላይ በአሸባሪዎች በግፍ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን አጽማቸው በሀገራቸው በክብር እንዲያርፍ ለማድረግ ከፕሬዚዳንት አል ሲ ሲ ጋር ተስማምተዋል። ለዚህም የግብጽ መንግስትና የጸጥታ ሃይሎች ለመተባበር ሙሉ ፈቃደኝነትና ዝግጅት መኖሩን ፕሬዚዳንቱ ገልፀውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ወንድም የሆነውን የግብጽ ህዝብ በፍጹም የሚጎዳ ነገር እንደማታደርግ አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ማልማት እንደምትችልና እንደሚገባትም የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ነገር ግን “ግብጽን ወይም ሱዳንን የመጉዳት እምነት በፍጹም እንደሌላት አረጋግጠዋል። በሌላ በኩል ዶክተር ዓቢይ በ100 የሹመት ቀናቸው ከሰሩት መካከል የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ የመጀመሪያ ተጋባዣቸው ማድረጋቸው ይጠቀሳል። ፖል ካጋሜም ግብዣውን ተቀብለው የሶስት ቀናት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ሀገራቱ ከዚህ በፊት የተፈራረሟቸውን ከ20 በላይ ስምምነቶች እንዲተገበሩ ተስማምተዋል። አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ሀገራቱን የሚያስተሳስሩ የልማት ስራዎች ላይ ተባብሮ ለመስራት ሁለቱ መሪዎች ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። ባለፉት 100 ቀናት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሶማሊያ ርዕሰ መዲና ሞቃዲሾም አቅንተው ነበር። ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላዚዝ ሙሐመድ ጋር በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው፥ የሀገራቱን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመቀየር እንሰራለን ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች በደምም ጭምር ዝምድና እንዳላቸው ጠቁመው ይህም ለአጋርነት ግብዓት መሆኑን ነው ያነሱት። ለዚህም ደግሞ አዲስ የአመራር ጥበብ መቃኘት እንደሚጠይቅ አስገንዝበው ይህም ሀገራቱ ለአካባቢው የሰላምና የምጣኔ ኃብታዊ ውህደት አስፈላጊነቱን ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ሶማሊያ ጠንካራ ሀገር መሆን እንደምትችል ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ከጎኗ ትቆማለች ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ከሚያደርጉ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች አልፈው በቅራኔ ውስጥ ያሉ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞችን ፊት ለፊት አገናኝተዋል። በዶክተር ዐቢይ ጥሪ መሰረት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያሪዲትና በደቡብ አፍሪካ የነበሩት የተቃዋሚ መሪ ዶክተር ሬክ ማቼር  ከሁለት ዓመት በኋለ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በ100 ቀናት ውስጥ ከምስራቅ አፍሪካ አልፈው በሳዑዲ ዓረቢያ እና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችም ጉብኝት አድርገዋል። በዚህ ጉብኝታቸው ኢትዮጵያ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ሃሳባቸውን ያንፀባረቁ ሲሆን በሀገራቱ ታስረው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም እንዲፈቱ አድርገዋል። በሳዑዲ ዓረቢያ ሆስፒታል ውስጥ በተፈጸመ የህክምና ስህተት የአልጋ ቁራኛ የነበረውን ታዳጊ መሀመድ አብዱል አዚዝ ጠይቀዋል፤ የታዳጊውን እናትም አግኝተው አበረታተዋል። መንግስት ዜጋውን ወደ ሀገሩ በመመለስ ለመደገፍ ሁሉንም ጥረት እንደሚያደርግም እና የሳዑዲ መንግስትም ለታዳጊው ካሳ እንዲከፍል ከልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን ጋር መስማማታቸው ይታወሳል። በሳዑዲ ዓረቢያ በነበራቸው ቆይታም 1 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እስረኞች እንዲፈቱና ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያደረጉበት ስራቸው በስኬት ይነሳል። ዶክተር ዐቢይ ከሳዑዲ ቀጥሎ ወደ ተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች  በማቅናት ከሀገሪቱ አልጋወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ጋር የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ዙሪያ መምክራቸውን እናስታውሳለን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጥሪ መሰረትም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች 118 ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ለመፍታት መስማማቷ ይታወቃል። በሌላ በኩል የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግብዣ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ሁለቱ መሪዎች የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና ኢትዮጵያ የ3 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንትና ድጋፍ የምታደርግበትን ስምምነት ተፈራርመዋል። 2 ቢሊዮኑ ኢንቨስትመንት ላይ የሚውል ሲሆን 1 ቢሊዮኑ ደግሞ የባንክ ተቀማጭ እንደሚሆን በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል። የተደረገው ስምምነት ለሀገራዊ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አልጋ ወራሽ አልናህያን በራሳቸው መኪና አንሸራሽረው ሽንጠ ረዥም ፈረስ በስጦታ ማበርከታቸውም በ100 ቀናት ውስጥ ያለፈ ትውስታችን ነው። ባለፉት 100 ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበቻው ጉዳዮች ላይ በስልክ መምከራቸው ይታወቃል። ሜይ የብሪታንያ መንግስት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ እንቅስቃሴ አጠናክራ እንድትቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀውላቸዋል። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜይ የኢትዮጵያ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦችን በይቅርታ ከእስር በመልቀቁ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ማይክ ፖምፔዮ ጋር በስልክ፣ ከቻይናው ህዝባዊ ኮንግረስ አፈ ጉባኤ እና ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሬውቨን ሪቭሊን እና ከሌሎችም መሪዎችና ዲፕሎማቶች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ያደረጓቸው ፍሬያማ ውይይቶችና ስምምነቶች ተጠቃሽ ናቸው። ከሁሉም በላይ ለ20 ዓመታት በጥል ሲተያዩ የነበሩ ሁለት ሀገራትን ወደ ሰላምና ወዳጅነት ያመጡበት ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን ስም ከፍ ያደርገዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ለዓመታት ከቆዩበት 20 ዓመታት የጦርነት እና የፍጥጫ ጉዞ ወጥተው ጠላትነታቸውን ሰርዘው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪ መሰረት የወዳጅነት ግንኙነት ጀምረዋል። ጠቅላይ  ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ባደረጉት ንግግር ከኤርትራ ጋር የሰላም ግንኙነት ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸው ይታወሳል። የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም የኢትዮጵያን የሰላም ጥሪ በመቀበል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሊሕ እና በፕሬዝዳንቱ አማካሪ የማነ ገብረ አብ የሚመራ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ልከዋል። ልዑኩ አዲስ አበባ ሲደርስም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድን ጨምሮ በርካታ የኪነጥበብ ሰዎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ደማቅ አቀባበል አድርገዋል። ባሳለፍነው እሁድ ወደ ኤርትራ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  እና በአስመራ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ሁለቱ መሪዎች ወደብ መጠቀምን ጨምሮ የሀገራቱን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመጀመር እንደዚሁም የሀገራቱ ዜጎች በሁለቱም ሀገራት በነፃነት እንዲንቀሳቀሱም ተስማምተዋል። በአዲስ አበባና አስመራ ኤምባሲዎች ይከፈታሉ ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የእስከዛሬው መኳረፍ ይበቃል በሚል ስሜት እንዲህ አሉ። "ዛሬ ደስታዬን ከፊቴ ማንበብ ትችላላችሁ፣ ከእንግዲህ በኋላ ጦርነት አናወሳም፣ ሰርተን የበደልነውን የሁለቱን አገር ህዝብ መካስ አለብን፤ "ከእንግዲህ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል ድንበር የለም ምክንያቱም ድንበሩ በፍቅር ተሰብሯል" ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፉት 100 ቀናት ከሀገር ውስጥ የመደመር ጉዞ ተነስተው፥ ቀጣናዊ ውህደትን መፍጠርና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ማጠናከር ያለመ ስራ አከናውነዋል። በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር ጉዞ በርካታ የዓለም አቀፍ መሪዎችን፣ መገናኛ ብዙሃንን እና የተንታኞችን ቀልብ ስቦ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል። በቀጣይ ሃምሌ 21 እና 22 ቀን 2010 ዓ.ም በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እንደሚያወያዩም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም