15 የተለያዩ ተቋማት ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

102

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጨምሮ 15 የተለያዩ ተቋማት በቅንጅት በመስራት ጥራት ያለው ምርት እና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣  ብሄራዊ  የጥራት  መሰረት ልማት ስር የሚገኙ ተቋማት፣  በኢትዮጵያ  ምግብና  መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና የንግድ ውድድር ሸማቾች ባለስልጣን ይገኙበታል።

ስምምነቱ በዘርፉ ቁልፍ ሚና ባላቸው አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሰራርና ጠንካራ አደረጃጀት እንዲኖር በማድረግ የገቢና የወጪ ምርቶች የሚጠበቅባቸውን መስፈርት እንዲያሟሉ ያስችላል ተብሏል።

የጥራት እና ቁጥጥር ስራውን ውጤታማ ከማድረግ በተጨማሪ በዘርፉ በተሰማሩ ተቋማት መካከል የተናበበ የአስራር ግልፅነት እና ተጠያቂነት ለማስፈን ያስችላል ተብሏል።

በስምምነት ሰነዱ ላይ ተቋማቱ በጋራ እና በተናጥል የሚተገብሯቸው ዋና ዋና ተግባራት ተዘርዝረዋል።

በንግድና ኢንዱስትሪ  ሚኒስቴር የጥራት፣ የንግድ አስራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ስምምነቱ ለተሻለ የምርት ጥራትና አገልግሎት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

በአለም አቀፍ እና በአፍሪካ ደረጃ ጥራት ያላቸው እና ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ለማቅረብ በጋራ መስራቱ አዋጭ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢኮኖሚ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን  ለማድረግ የምርት  ጥራትና  አገልግሎት ላይ ትኩረት ማድረግም ጊዜው የሚጠይቀው አይነተኛ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለ መኮንን እንዳሉትም የጋራ ስምምነቱ በደረጃ አስጣጥ ወቅት  ያለውን ክፍተት  ለማስወገድ  የሚያግዝ ነው።

አምራችና አገልግሎት  ሰጪ ተቋማት  ጥራት ያለው ምርት እንዳያቀርቡ ያላደረጋቸው ምክንያት በጥናት መለየት ይገባል ነው ያሉት።

በመሆኑም አምራቾች ጥራት ያለው ምርት ማቅረብ እንዲችሉ በደረጃ መዳቢ እና ጥራት ተቆጣጣሪ ተቋማት ድጋፍ እና ክትትል የሚደረግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት በተለይ በጥራት መጓደል ምክንያት በወጭ ንግድ ላይ የሚስተዋለው ችግር እንደሚቃለል እምነት አሳድሯል።

ከወጭ ንግድ በተጨማሪ በሌሎች የንግድ ልውውጦችና የገበያ ሰንሰለቶች ላይ የሚታየውን ችግር እንደሚፈታም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም