በቀጣዮቹ ዓመታት ለመንገድ ጥራት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ተገለጸ

53

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) በቀጣዮቹ ዓመታት ለመንገድ ተደራሽነት ብቻ ሳይሆን ለጥራትም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።

በመንገድ ልማት የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ከ1 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ብር በላይ ለመንገድ ልማት እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር በስሩ ካሉ 10 ተጠሪ ተቋማት ጋር በየተቋማቱ ዝርዝር የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት በቢሾፍቱ እያካሄደ ነው።

በውይይቱ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የ10 ዓመት መሪ እቅዱን አቅርቧል።

በእቅዱ የመንገድ ዘርፉ ለኢኮኖሚው ትልቅ ድርሻ ያላቸውን የግብርና፣ የነዳጅ፣ የቱሪዝም እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚደግፍ ስራ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጿል።

በመንገድ ግንባታ ዘርፍ አዲሰ ምዕራፍ እንዲመጣ የመንገዶችን ኪሎ ሜትር መጨመር ብቻ ሳይሆን በባለቤትነት የሚመራበትን የተቋማት ግንባታ እና በዘርፉ ያሉ አዋጆችን መከለስ እንደሚገባ ተጠቅሷል።

በእቅዱ አሁን ያለውን ከ130 እሰከ 140 ኪሎ ሜትር አጠቃላይ የአገሪቱን የመንገድ ሽፋን ወደ 225 ኪሎ ሜትር ከፍ ለማድረግ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

ከዚህ የበጀት የድጎማ፣ የመሰረተ ልማት አሰጣጥ ስርዓቱንም መልሶ መፈተሽ እንደሚገባና የተቋምና የባለሙያ አቅም ግንባታም እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።

በአጠቃላይ በመንገድ ዘርፉ መልካም ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም የጥራት ችግር ግን ትልቁ አጀንዳ በመሆኑ እዚህ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም ነው የተነሳው።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ከዚህ ቀደም በመንገድ ልማት ዘርፍ ተደራሽነት ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

ከጥራት ጋር የተያያዙ ችግሮች በዘርፉ በስፋት የሚስተዋሉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የጥራት እና የፍትሃዊነት ጉዳይ አሁን ቅድሚያ የሚሰጣቸው አጀንዳዎች መሆኑን አረጋግጠዋል።

አሁን ላይ በበቂ ጥናት እና ዝግጅት እንዲሁም አዋጭነቱ ታይቶ ጥራት እና ፍጥነት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ እንዳሉት እንደ አገር በመንገድ ዘርፉ በርካታ ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው፤ የጥራት ችግር ግን ትልቁ አጀንዳ ነው ብለዋል።

የዘርፉን ልማት ለማሳደግ የተቋማትን አቅም ግንባታ እና የባለሙያዎችን ክህሎት ማሳደግ እንደሚገባ አንስተዋል።

ጥራት ያለው መንገድ ለመስራት የቁጥጥርን አቅም ማሳደግ እንደሚጋባ ያነሱት ኢንጅነር ሀብታሙ ይህንን ደግሞ የመንገዶች ባለስልጣን ብቻውን ማድረግ የሚችል ባለመሆኑ እስከ ወረዳ ድረስ ተቋም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።

በመንገድ ዘርፉ አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ እንድትሰለፍና የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን በመንግስት ብቻ ሳይሆን የግሉ ዘርፍም እንዲሰማራ ጥሪ እንደሚደረግ አንስተዋል።

ይህ ደግሞ መንግስት ብቻ ለዘርፉ የሚያፈሰውን መዋለ ንዋይ ጫና እንደሚቀንሰው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም