የለውጥ ጉዞውን ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ተጀመረ

112

ሀዋሳ፣ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) የለውጥ ጉዞውን ማስቀጠል በሚቻልበት ዙሪያ የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተጀመረ።

የክልሉ  ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አክሊሉ ታደሰ እንደገለጹት ለሁለት ቀናት የሚቆየው ይሄው ውይይት ከዚህ በፊት በተመሳሳይ የተካሄዱ ሁለት መድረኮች የቀጠለ ነው።

አመራሮቹ በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት እንደሚወያዩ  ያመለከቱት  አቶ አክሊሉ በዋናነት ግን ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል  የተካሄደው  የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል በሚቻልበት ላይ እንደሚያተኩር አስረድተዋል።

ለውጡን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ጉዳዮችን ለይቶ በመታገል ረገድ የጋራ መግባባት ለመፍጠርም እንደሆነ ገልጸዋል።

የዜጉች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ፣ የህግ የበላይነት ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ፣ አንድነቷ የፀና ህብረ-ብሔራዊት ሀገር የመገንባት ሂደት  ላይም ምክከር ይደረጋል ብለዋል።

ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮችም በስፋት እንደሚቃኙ አመልክተው፤  በደቡብ ክልል ህዝቦች የሚያነሷቸው የአደረጃጀት ጥያቄዎች ሠላማዊና ሕገ-መንግስታዊ ሂደታቸውን ጠብቀው በሚመለሱበት አግባብ ዙሪያም   በጥልቀት  ውይይት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

ከለውጡ በኋላ የውስጥ ችግር ሆኖ የቀጠለው የአንዳንድ አመራሮች የህዝቦችን ጥያቄ ተቋማዊ አድርጎ በአግባቡ ምላሽ እንዲያገኝ ከመጣር ይልቅ ባልተፈለገ አቅጣጫ በመምራታቸው እንደሆነ  ጠቅሰው፤  በአመራሩ መካከል ይህንን በሚያርም መልኩ የጋራ አቋም መፍጠርም  የመድረኩ ሌላኛው ዓላማ እንደሆነም አስረድተዋል።

በመድረኩ  178 በክልል ደረጃ ያሉ  አመራሮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም