የእምነት አባቶች ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚነሱ ግጭቶችን እንዲከላከሉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የእምነት አባቶች ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚነሱ ግጭቶችን እንዲከላከሉ ጥሪ ቀረበ
50
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) የእምነት አባቶች ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚነሱ ግጭቶችን በመከላከል ረገድ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የሰላም ሚኒስቴር ዛሬ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ 12ኛ መደበኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ነው።
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሃይማኖት አባቶች አገራዊ ሰላምና ደህንነትን በማስፈን ሚናቸው የጎላ ነው።
በመሆኑም በተከታዮቻቸው ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም ግጭትን እንዳይከሰትና አንድነት እንዲያጠናከር ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ሕዝብን በመከፋፈል ለግጭትና ብጥብጥ የሚጋብዙ ጽንፈኞችን በመከላከል ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የእምነት አባቶች በኢትዮጵያ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሲከሰት ምዕመናን ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በቤታቸው ሆነው እንዲከታተሉ በማድረግ ውጤታማ ተግባር መፈጸማቸውን ወይዘሮ ሙፈሪያት መስክረዋል።
የሃይማኖት አባቶች ባላቸው ተሰሚነት በአስተምህሮዎቻቸው ግጭቶችን የሃይማኖት ቅርጽ ለማስያዝ የሚሞክሩ አካላትን እንዲከላከሉ ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በየሃይማኖት ተቋማት አባቶች በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት ለመከላከል ተከታዮቻቸውን በማስተማርና በመገሰጽ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።