በአዲስ አበባ ከተማ 102 ህገ-ወጥ ሽጉጦችና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስራ ዋሉ

41

አዲስ አበባ (ኢዜአ) 27/2012 በአዲስ አበባ ከተማ 102 ህገ-ወጥ ሽጉጦችና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስራ ማዋሉን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

ወጣቶች በሀሰት መረጃ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በሚደረግ ሙከራ ሳይዘናጉ የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲጠብቁም ጥሪ ቀርቧል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ጀይላን አብዲ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በመዲናይቱ በተለምዶ ኮልፌ 18 ማዞሪያ እና ሰሜን ማዘጋጃ’ በሚባሉ አካባቢዎች ነው ህገወጥ መሳሪያዎቹ የተያዙት።

መሳሪያዎቹን ተጠርጣሪው ግለሰብ በተከራይዋቸው ቤቶች ውስጥ  መያዛቸውን ገልጸዋል።

በተደረገው ፍተሻም 102 ሽጉጦች 399 ጥይቶችና ሌሎች በርካታ የጦር መሳሪያ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የተናገሩት።

ተጠርጣሪው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት መሆኑን በመጠቆም።

ተጠርጣሪው በሰጡት ቃል መሳሪያዎቹ መነሻቸውን ሱዳን አድርገው በጎንደር በኩል አዲስ አበባ እንደገቡም  መናገራቸውንም አቶ ጀይላን ገልጸዋል።

ህገወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ቤት በመከራየት ወንጀሉን እንደሚፈጽሙ ጠቅሰው፤ ከዚህ አንጻር አከራዮች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በህገወጥ መንገድ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሽጉጦች የተገኙባቸው ቤቶች አከራዮች ስለተከራዮቻቸው ማንነት እንደማያውቁ መግለጻቸውን ለአብነት በመጥቀስ።

በተያያዘ ዜና በኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ድጋሜ ሁከት ለመቀስቀስ የሚጥሩ አካላት እንዳሉ አቶ ጀይላን ተናግረዋል።

እነዚህ አካላት በዋናነት ምስሎችን ‘በፎቶ ሾፕ’ በማቀናበርና ከለውጡ በፊት የተደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አሁን እንደተከናወኑ በማስመሰል ህዝብን እያደናገሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይህን እኩይ ተግባር ሊገነዘብ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

እነዚህ አካላት የጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት ግድ ሳይሰጣቸው በተደጋጋሚ አድማዎችንና ሁከቶችን ሲጠሩ መቆየታቸውን አውስተዋል።

”ነገር ግን ወጣቶች ሰላም የሚያመጣላቸውን ጥቅም በመገንዘብ ለእኩይ ጥሪያቸው ምላሽ አልሰጧቸውም” ብለዋል።

በመሆኑም ወጣቶች ምንጫቸው ከየት እንደሆነ በማይታወቁ የሀሰት መረጃዋች ሳይዘናጉ ሰላማቸውን እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት አገርን በሁከት ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በህግ ጥላ ስር የማዋሉን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ጀይላን ተናግረዋል።

የጸጥታ መዋቅሩ የዜጎችን ድህንነት ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑንም ነው የገለጹት።