በኦሮሚያ ክልል በተካሄደ ኦዲት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ የባከነ ገንዘብ ተገኘ

114
አዳማ ሐምሌ 4/2010 በኦሮሚያ ክልል በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በተካሄደ ኦዲት ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ የባከነ ገንዘብ ማግኘቱን የክልሉ ጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት ገለጠ። የኦዲት መስሪያ ቤቱ 2010 ዓ.ም የበጀት አመት በ462 የክልሉ የመንግስት ተቋማት ላይ የፋይናንስና ሂሳብ አሰራት፣ የንብረት አያያዝና አስተዳደር፣ የዓይነትና የተፈጥሮ ሀብት ኦዲት ማድረጉን ዋና ኦዲተር አቶ ኤሌማ ቃምጴ ለጨፌው ባቀረቡት ሪፖርት ገልጠዋል። የፋይናንስና የሂሳብ አስተዳደር ኦዲት ክንውን በ326 ተቋማት ላይ የተከናወነ ሲሆን ከ140 በላይ በሚሆኑት ላይ ደግሞ የንብረት አስተዳደርና አያያዝ የተፈጥሮ ሃብት አጠባባቅ ኦዲት ተደርጓል። በዚህም በበጀት አመቱ ዕቅድ 92 በመቶ ማሳካቱን ተናግረዋል። የፋይናንስ ኦዲት ከተደረገባቸው ተቋማት ውስጥ 280 የሚሆኑት ጥሩ የሂሳብ አያያዝ ያላቸውና ትንሽ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ሃሳብ የተሰጠባቸው ሲሆን 45 የሚሆኑት ደግሞ ውስብስብ ችግር ያለባቸው መሆኑን ዋና ኦዲተሩ አመልክተዋል። በኦዲት ወቅት በዋናነት ከታዩት ችግሮች መካከል የግብና ታክስ አሰባሰብ፣ የመሬት ሊዝ፣ ኪራይና ታሪፍ መቀነስ የወጪ አስተዳደር ችግር የተከፋይና ተቀማጭ ሂሳብ አሰራር ክፍተት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ከኦዲት ግኝቱ ውስጥ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ማስረጃ እንዲቀርብበትና  እንዲወራረድ ሃሳብ  የተሰጠ ቢሆንም  እስካሁን  የተወራረደው  88 ሚሊዮን ብር ብቻ  በመሆኑ ሃብቱ ወደ መንግስት ካዝና  እንዲመለስና አጥፊዎቹ ለህግ እንዲቀርቡ አቅጣጫ መሰጠቱን አቶ አማን አመልክተዋል። በተመሳሳይ 512 ሚሊዮን ብር ያለ አግባብ ወጪ የሆነ  አንዲመለስ በተደረገ ጥረት 87 ሚሊዮን ብር ብቻ መመለሱን አመልክተው መንግስትና የምክርቤቱ አባላት ሃብቱ እንዲመለስ በጋራ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ የኦዲት ግኝቱ በዋናነት ከ2007 እስከ 2009  ዓ.ም የተሸፈነ መሆኑን ዋና  ኦዲተሩ አመልክተዋል። የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የተመዘበረውና የባከነው የህዝብ ሃብት እንዲመለስ ብሎም  አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ የመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነት  የታከለበት  እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡ በተመሳሳይ በልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚፈፀም ምዝበራና ሙስና መቋጫ እንዲያገኝ የምክር ቤቱ አባላት የሚያደርጉትን ድጋፍ፣ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡ የኦዲት ግኝቱ ውጤታማ እንዲሆን የአስፈፃሚው አካል ትኩረት እንዲያገኝና ሃብቱ እንዲመለስ መንግስት መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ የኦሮሚያ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶለሳ ገደፋ እንደገለፁት አብዛኛው የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሂሳብ አሰራርና አያያዝ ላይ መሻሻሎች መታየቱን ተናግረዋል። ''ችግሩ በዋናነት የሚታየው በዞንና የከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በመሆኑ ይህን ለማስተካከል እንሰራለን'' ብለዋል። ባለፈው በጀት አመት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም