የችግኝ ተከላው የአየር መዛባትን በማስተካከል የኃይል አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ያግዛል

55

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 27/2012 (ኢዜአ) የችግኝ ተከላ መርሃግብር የአየር መዛባትን በማስተካከል በኢንዱስትሪዎች የሚስተዋለውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አመራሮችና ሠራተኞች በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዛሬ ከ2 ሺህ በላይ የማንጎና የአቮካዶ ችግኞችን ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ በዚህ ወቅት እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር መጠናከር የአየር መዛባትን ለማስተካከል ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ይህም በአየር መዛባት ምክንያት በሚፈጠር የኃይል አቅርቦት እጥረት ኢንዱስትሪዎች የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

በመሆኑም አመራሩ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ሠራተኞችና ደንበኞች የችግኝ ተከላ መርሃግብሩን ከሌላው በበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነው ወይዘሮ የሺመቤት ያሳሰቡት።

“የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች የተከላ መርሃ ግብሩን ከተቋሙ ተልዕኮ አንጻር እንጂ እንደተጨማሪ ሥራ መመልከት የለባቸውም" ብለዋል።

"ኢንዱስትሪዎች ለአፈጻጸም ድክመታቸው የኃይል አቅርቦት እጥረትን በየጊዜው እንደምክንያት ያነሳሉ" ያሉት ወይዘሮ የሺእመቤት፣ ለአረንጓዴ ልማቱ ተገቢ ትኩረት መስጠት በኃይል አቅርቦት በኩል አቅምን ለማሳደግ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

"የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ችግኝ ከመትከል ባለፈ ከችግኞች ሊገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ታሳቢ ያደረገ ነው" ያሉት ደግሞ በድርጅቱ የግብዓት ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ንጉሴ ገብረማሪያም ናቸው ።

የአረንጓዴ ልማት መርሃግብሩን ማጠናከር የአየር መዛባትን በመከላከል የኃይል ማመንጫዎች በቂ የዝናብ ውሃ እንዲይዙ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪዎች በመገኙበት አካባቢ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን መትከል ከእዕዋቱ ጣምራ ጥቅምን እንደሚያስገኝም አቶ ንጉሴ አመልክተዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ በሁሉም የድርጅቱ ቅርንጫፎች የሚገኙ ሠራተኞችን በማንቀሳቀስ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከ100 ሺህ በላይ ችግኞችን የመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል።

በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃግብር በአዲስ አበባ ከሚገኙ 12 የድርጅቱ ቅርንጫፎች የተውጣጡ ከ350 በላይ አመራሮችና ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም