ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ጉዳዮች አንድ የጋራ አቋም መያዝ ይገባል

71

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 27/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ጉዳዮች የጋራ አቋም ሊይዙ እንደሚገባ ተገለጸ።

መንግስት የትግራይ ህዝብን አደጋ ውስጥ የሚከቱ እንቅሰቃሴዎችን በዝምታ መመልከት የለበትም ተብሏል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና የፌዴራሊዝም ምሁር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋና የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በኮሮናቫይረስ መከላከልና በህዳሴው ግድብ ላይ የታየውን አንድነትና መነሳሳት የዜጎችን ሰብዓዊ መብትና የህግ የበላይነት እንዲከበር ለማድረግም መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የህግ የበላይነትንና የኢትዮጵያዊያንን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል እንደሌለበት ተናግረዋል።

ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው በትግራይ የሚደረገው ምርጫ የፌዴራሉንና የክልሉን ሕገ መንግስት የጣሰ ድርጊት እንደሆነ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ውስጥ ባሉ ወገኖች ላይ የሚደርሱ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ የመብት  ጥሰቶች፣ የተጋረጠውን የኮሮናቫይረስ አደጋ ከመከላከል አንጻር ታይቶ ከወዲሁ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ''ህወሃት ምርጫ ለማድረግ የሚያደርገው ዝግጅት የትግራይን ህዝብ የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል'' ብለዋል።

ምርጫው ከተካሄደ የፌዴራል መንግስትንም የሚያስጠይቅ እንደሆነም አመልክተዋል።

እንደ እገር እስካሁን የገጠሙ ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ሁሉም ነቅቶ በመጠበቅ የለማች አገር ለትውልድ ማስረከብ እንደሚገባ የኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ተናግረዋል።

እስካሁን የአገሪቱን ልማትና እድገት ሲፈታተኑ የነበሩ ሃይሎች ቀጣይም ከድርጊታቸው ላይታቀቡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ይህንን ችግር መከላከል የሚቻለው መንግስት ከሚያደርገው የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ ጎን ለጎን እያንዳንዱ ዜጋ ስለ አገሩ ጉዳይ 'ያገባኛል' ብሎ በአንድነት ሲቆም መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዜጎች ሰብዓዊ መብት፣ በአገራዊ ሉአላዊነትና አገርን አንድ በሚያደርጉ ልማቶች ላይ ሁሉም መሳተፍ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም