የአዲስ አበባን የመሬት ሃብት ለማወቅ የሚያስችል የኦዲትና ምዝገባ ሊከናወን ነው

93

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 27/2012 (ኢዜአ) በዘንድሮው በጀት ዓመት የመዲናዋን የመሬት ሀብት ለማወቅ የሚያስችል የመሬት ኦዲትና ምዝገባ የሚከናወን መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ሰባተኛ ዓመት ሦስተኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው እለት ማካሄድ ጀምሯል።

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የ2012 ዓ.ም የእቅድ አፈጻጸምና የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ያካተተ ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል።

በበጀት ዓመቱ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ሥራዎችን በዝርዝር ያስቀመጡ ሲሆን፣ በዋነኛው የመሬት ኦዲት ሥራን ጠቅሰዋል።

የከተማ ትልቁ ሀብት መሬት እንደመሆኑ በተደራጀ መረጃና በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ መሬቶች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ የሚያስችል የመሬት ኦዲትና ምዝገባ ስራ ይከናወናል ብለዋል።

በመሬት ኦዲቱ አማካኝነት ያለ አግባብ ጥቅም ላይ የዋሉና ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ የተቀመጡ መሬቶች ለሌሎች የልማት ሥራዎች እንደሚውሉ አመልክተዋል።

በተጠቀሱት ምክንያቶች የተያዙ መሬቶች በመዲናዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ እንደ አንድ አማራጭ እንደሚጠቀምበትም ገልጸዋል።

በመሬት ኦዲት የተገኙ ቦታዎችን የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ተመዝግበው ለዓመታት እየጠበቁ ላሉ ዜጎች በማህበር ተደራጅተው የጋራ መኖሪያ ህንጻ እንዲገነቡ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ እንደሚከናወንም ነው ኢንጂነር ታከለ ያስረዱት።

የመሬት ኦዲት እቅዱ ዋነኛ ዓላማ በከተማዋ የሚታየውን ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ለመከላከል ያለመ መሆኑን አብራርትዋል።

ለህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ዋነኛ ተጋላጭ አርሶ አደሮች መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ከንቲባው የመሬት ይዞታ ተለይቶ ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ይዘጋጅላቸዋል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በመዲናዋ የተጀመሩ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችም በእቅዳቸው መሰረት ይጠናቀቃሉም ነው ያሉት በሪፖርታቸው።

የሸገር ቤተ-መጻህፍት ግንባታና ከመስቀል አደባባይ እስከ ማዘጋጃ ቤት የሚሰራው ፕሮጄክት ተጠናቀው ወደ ሥራ የሚገቡ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ኮሮናቫይረስን በመከላከል ረገድ በሚስተዋለው የማህበረሰብ ጥንቃቄ ማነስ ለቫይረሱ ሥርጭት መስፋፋት አስጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ሥርጭቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

አገራዊ ለውጡን በተሻለ መልኩ እንዲቀጥል በማድረግ  በከተማዋ እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ለማውረድና ለውጡ ተቋማዊ እንዲሆን የማድረግ ሥራም ይከናወናል ብለዋል።

ለውጡን በተሻለ መልኩ መምራትና ለመዲናዋ ነዋሪ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አመራሮችን የማደራጀትና የማስፈጸም አቅማቸውን በማጎልበት አገልግሎት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣትም ይሰራል ብለዋል።

በከተማዋ ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት የተለያዩ የሥራ እና የፋይናንስ አማራጮችን በማስፋት ለ280 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል ብለዋል።

የከተማ ግብርናን ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ እንደ አማራጭ መያዙንም ገልጸዋል።

የታክስና የግብር መሰረትን በማስፋት በበጀት ዓመቱ 48 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷልም ብለዋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለተቀዛቀዘው የኤኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ የማነቃቂያ ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍ የጤና መሰረተ ልማቶችን መገንባትና የሰው ኃይል ልማት ሥራ እንዲሁም የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ተግባር በበጀት ዓመቱ ከሚሰሩ ተግባራት መካከል መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ ከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።

የኑሮ ውድነትና ህገ-ወጥ ንግድን መቆጣጠር፣ የከተማውን ሰላም የማስከበር፣ የውሃና መብራት ሥርጭት ፍትሐዊነት እንዲረጋገጥ ማድረግ፣ የቅሬታዎች አፈታት ሥርዓትን ማሻሻልና የመሬት ወረራና ህገ-ወጥ ግንባታ ላይ እርምጃ መውሰድ ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም