ሕገወጥ የንግድ አሰራር ውስጥ በተገኙ የመዲናዋ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዶባቸዋል - ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ

58

አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2012 (ኢዜአ) በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ሕገወጥ የንግድ ስራ ውስጥ በተገኙ የመዲናዋ ነጋዴዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እንደተወሰዱባቸው ተገለጸ።

ከተወሰዱት ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ማስጠንቀቂያ፣ የንግድ ፈቃድ ስረዛና እገዳ፣ ከንግድ ትስስር ማስወጣትና የንግድ ድርጅት ማሸግ ይገኙባቸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 7ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ማካሄድ ጀምሯል።

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የአስተዳደሩን የ2012 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸምና የ2013 ዓ.ም ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ያካተተ ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል።

በሪፖርቱ ከተነሱ ሀሳቦች መካከል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በንግዱ ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች ይጠቀሳል።

ኢንጂነር ታከለ ኡማ የመዲናዋ የንግድ ስርዓት ሰፊ መሆኑንና ለመቆጣጠርም ጠንካራ መዋቅራዊ ስርዓትና ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።

የንግድ ስርዓቱ ፍትሃዊና ተወዳዳሪ እንዲሆን የማድረግና ለከተማዋ ኢኮኖሚ ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጥ የማስቻል ስራዎች በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መከወናቸውንም ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተቋማትና ግለሰቦችን ወደ ሕጋዊ መንገድ የመመለስ፤ ለሕግ ባልተገዙት ላይ ደግሞ እርምጃ የመውሰድ ስራ መሰራቱን ነው የገለጹት።

በዚሁ መሰረት ለ20 ሺህ ድርጅቶች ከድርጊታቸው እንዲታረሙ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው፤ ከ13 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶችም እንዲታሸጉ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

272 የንግድ ፈቃድ መሰረዙንና የ186ቱ መታገዱን እንዲሁም 262 የንግድ ድርጅቶች ከንግድ ትስስር እንዲወጡ መደረጉን ነው ምክትል ከንቲባው ያብራሩት።

ከተፈቀደው ሚዛን በታች ምርቶችን ሲሸጡ የነበሩ 346 ነጋዴዎች ላይም ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።

የንግድ ስርዓቱን ሕግ በማስከበር ብቻ ማስተካከልና ፍትሃዊ ማድረግ አይቻልም ያሉት ኢንጂነር ታከለ ስርዓቱን ያሻሽላሉ የተባሉ የመፍትሔ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩንም ገልጸዋል።

የንግድ እሴት ሰንሰለቱን ማስተካከል፣ የሰብል ምርቶች አቅርቦት፣ የቁም ከብት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማዕከላትን ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅና የአቅርቦት ችግሩን መፍታት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል ምክትል ከንቲባው በሪፖርታቸው።

የንግድ እንቅስቃሴዎች በውስን ቦታዎች እንዳይገደቡ ለማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች ዘመናዊ የንግድ ማዕከላት የመገንባት ስራ በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት መጀመሩን ጠቅሰዋል።

በመዲናዋ ያለውን የዳቦና የዘይት አቅርቦት ችግር ለመፍታትም የሸገር ዳቦና ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ ንረትን የመቆጣጠር ስራ እንደሚከናወንም አመልክተዋል።

ከታክስ ጋር በተያያዘ የታክስ ማሻሻያዎች የመዋቅር ለውጥ በማድረግ ውዝፍ የታክስ ዕዳ ማቅለያ በማድረግ በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ ምንጮች 42 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንም ጠቁመዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ቀጥታና ቀጥታ ካልሆነ ታክስ እንዲሁም የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን የሚያካትት እንደሆነም አክለዋል።

ይህ ገቢ ከ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ነው ኢንጂነር ታከለ ያስረዱት።

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ250 ሺህ በላይ ሰዎችም የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።

የዕደ-ጥበብ ውጤቶች ስራን በማስፋት ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚሆኑ ተግባራትም ተከናውነዋል።

በከተማ ግብርናም 600 ሄክታር መሬት በማዘጋጀት በቶሎ የሚደርሱ አትክልቶችን በማምረት የምግብ አቅርቦት ችግርን መፍታት የሚያስችል ስራ ተጀምሯል።

የሸክላና ሸማ ስራዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው በማድረግ የእንስራ ሸክላ ማዕከል ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ አውስተዋል።

የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል 96 ሺህ የ20/80፣ 29 ሺህ የ40/60 በድምሩ 125 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን የግሉን ዘርፍ በግንባታው የሚያሳትፉ ስራዎችም እየተሰሩ ነው።

መዲናዋን የሚመጥኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ በሚፈለገው ጥራት ተሰርተው እየተጠናቀቁ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም አገራዊ የፕሮጀክት የመፈጸም አቅምን ያሳደገና አዲስ ልምድና ተሞክሮ የተወሰደበት መሆኑንም አንስተዋል።

የውሃ፣ የኤሌክትሪክና የትራንስፖርት አቅርቦት ችግሮችን መፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እንደተሰራባቸውና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

ተማሪዎች ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያደርጉ የምግብና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፉ ተቋማዊ መሰረት እንዲኖረው ኤጀንሲ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩንም ነው ያወሱት።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 7ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባዔ እስከ ነገ የሚዘልቅ ነው።

በጉባዔው የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የኦዲት እንዲሁም የከተማዋ ፍርድ ቤቶች ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል ተብሏል።

በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የተጠሪነት ጉዳይ የቀረበ ሞሽንም ውይይት ተደርጎበት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።

በምክር ቤቱ አንድ አባል ያለመከሰስ መብት ላይ ውይይት እንደሚደረግና ውሳኔ እንደሚተላለፍ፤ ሹመቶችም ቀርበው እንደሚጸድቁ ከጉባዔው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም