በዓለም የወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር በሶስት ሺህ ሜትር ሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ

69
አዲስ አበባ ሐምሌ 4/2010 በፊንላንድ ቴምፔሬ 17ኛ የዓለም ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች የአትሌቲክስ ውድድር ዛሬ የሶስት ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል። ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ55 ደቂቃ በሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መሰሉ በርሄና ጽጌ ገብረሰላማ ይሳተፋሉ። አትሌት መሰሉ በርሄ ባለፈው ዓመት በአልጄሪያ በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ የታዳጊዎች አትሌቲክስ ውድድር በሶስት ሺህ ሜትር 9 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ ከ10 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ያስመዘገበችው ውጤት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷ ነው። ሌላኛዋ ተወዳዳሪ ጽጌ ገብረሰላማ በግንቦት 2010 ዓ.ም አሰላ በተካሄደው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሶስት ሺህ ሜትር ውድድር አሸናፊ መሆኗ የሚታወስ ነው። በውድድሩ የገባችበት 9 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ ከ38 ማይክሮ ሰከንድ በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷ ነው። የኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች ውድድሩን የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ማግኘታቸውን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በድረ-ገጹ አስነብቧል። ከሶስት ሺህ ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ውድድር በተጨማሪ ዛሬ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የ400 ሜትርና የ800 ሜትር ሴቶች የመጨረሻ የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ከቀኑ 11 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ በሚካሄደው የ800 ሜትር ሴቶች በምድብ አንድ አትሌት ደርቤ ወልተጂ፤ በምድብ ሁለት አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ይወዳደራሉ። ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ትናንት ባደረጉት የመጀመሪያ ማጣሪያ ውድድር ከየምድባቸው አንደኛ በመውጣት ለዛሬው ውድድር ያለፉ ሲሆን አትሌቶቹ በዛሬው ማጣሪያ ከየምድባቸው አንደኛ ወይም ሁለተኛ ከወጡ ነገ ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ48 ደቂቃ በሚካሄደው የፍጻሜ ውደድር ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ። ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ25 በሚካሄደው የ400 ሜትር ሴቶች የመጨረሻ የማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፍሬህይወት ወንዴ ትሳተፋለች። በውድድሩ አንደኛ ወይም ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ካጠናቀቀች ነገ ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር ታልፋለች ማለት ነው። ዛሬ በወንዶች የጦር ውርወራ፣ የርዝመት ዝላይና የሴቶች አሎሎ ውርወራ ፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ። በመክፈጫው ዕለት  በተካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያ ሁለት የነሐስና አንድ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች። በአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር  እጅጋየሁ ታዬና ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር ሁለተኛና ሶስተኛ የወጡ ሲሆን በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ አትሌት በሪሁ አረጋዊ ሶስተኛ ሆኗል። በሁለቱም ውድድሮች ኬንያ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። የዓለም ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች የአትሌቲክስ ውድድር እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም