ስለሕዳሴው ግድብ ለዓለም ህዝብ እያሳወቁ መሆናቸውን በሳዑዲ አረቢያ የተወለዱ ወጣቶች ገለጹ

70

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 27/2012 (ኢዜአ) የሕዳሴው ግድብን አስመልክቶ ትክክለኛ መረጃዎችን በአረበኛ ቋንቋ ለዓለም ህዝብ እያሳወቁ መሆናቸውን በሳዑዲ አረቢያ የተወለዱ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ገለጹ።

በሳዑዲ አረቢያ ተወልደው ያደጉትና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የሕዳሴውን ግድበ አስመልክቶ በአረበኛ ቋንቋ መረጃዎችን እያሰራጩ መሆናቸውን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ከተማ ተወልዳ ያደገችው የ19 ዓመቷ ከድጃ አህመድ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቷ በፊት በሕዳሴው ግድብ ላይ የነበራት መረጃ አሁን ካላት ፍጹም የተለየ እንደነበር ተናግራለች።

ከመጠሪያው ጀምሮ ስለ ዓባይ ወንዝ እየሰማች ያደገችው እውነታና አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የተለያየ መሆኑንም  ገልጻለች።

እንደወጣቷ ገለጻ በግድቡ ዙሪያ ያለውን እውነታ በአረበኛ ቋንቋ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ለዓለም ለማሳወቅ ከጓደኞቿ ጋር ሆና በጋራ እየሰሩ ነው። 

ከሳዑዲ አረቢያ የመጡ የተለያዩ ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት በዓባይ ግድብ ላይ እየሰሙ ያደጉትን የተሳሳተ መረጃ ለማስተካከል ሥራ መጀመራቸውን የተናገረው ደግሞ ወጣት ሱህል ቡሽራ ነው።

አስካሁንም በአረበኛ፣ አማርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች የሦስት ደቂቃ ፕሮግራም ሰርተው በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን ነው የገለጸው።

የዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዓመት የማናጅመንት ተማሪ የሆነችው ያስሚን ሰኢድ በበኩሏ፣ በኢትዮጵያ በኩል የሕዳሴውን ግድብ አስመልክቶ በአረበኛ ቋንቋ መረጃዎችን የማሰራጨት እጥረት እንዳለ መታዘቧን ገልጿለች።

በመሆኑም ስለግድቡ ትክክለኛ እውነታዎችን በማሰባሰብ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በአረበኛ ቋንቋ እያሰራጨች መሆኑን ተናግራለች።

በቀጣይም ትውልዳቸው በአረቡ ዓለም የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን በማስተባበር በግድቡ ዙሪያ ለአገራቸው ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚሰሩ ገልጻለች።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ የሆነችው ሩማን አብዱራዛቅ በበኩሏ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የአረበኛ ቋንቋን ጨምሮ በተለያዩ ቋንቃዎች መረጃዎችን በማሰራጨት የድርሻዋን እንደምትወጣ አስታውቃለች።

ወጣቶቹ ግድቡ "የኔ ነው፤ እስኪጠናቀቅ ድረስም በምንችለው ሁሉ የድርሻችንን እናበረክታለን” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን አጠቃላይ የግንባታ ሥራውም በአሁኑ ወቅት 74 በመቶ ላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም