ኢትዮጵያ ዓባይን በፍትሃዊነት መጠቀም የሚያስችላትን ውይይት ማድረግ አለባት

75

አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ የውሃ ሙሌት ሳትዘናጋ በቀጣይ የዓባይን ወንዝ በፍትሃዊነት መጠቀም የሚያስችላትን ውይይት ማድረግ እንዳለባት ምሁራን ገለጹ።

በኢትዮጵያ የውስጥ አንድነትና የዲፕሎማሲ አቅምን መገንባት ከተቻለ "እውነት ከኢትዮጵያ ጋር ስለሆነ ታሸንፋለች" ብለዋል ምሁራኑ።

በአፍሪካ 11 አገሮችን አቆራርጦ መዳረሻውን ሜዲተራኒያን ባህር የሚያደርገው ታላቁ የዓባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ 'እዚህ ግባ' የሚባል ጥቅም ሳይሰጥ ዘመናትን አስቆጥሯል።

ኢትዮጵያ በወንዙ ላይ ያላት ድርሻ 86 በመቶ ያህል ቢሆንም ሱዳንና ግብጽ ሲበለጽጉበት ኖረዋል።

እንደአውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1929 እና 1959 ግብጽ ከእንግሊዝ ጋር በፈረመችው መርህ አልባ የቅኝ ግዛት ስምምነት ዛሬም በዓባይ ላይ ብቸኛዋ "አዛዥ" መሆንን ትፈልጋለች።

በኢትዮ-አረብ የጥናትና ምርምር ባለሙያ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት አቋም ለማንጸባረቅ ጠንካራ የዲፕሎማሲ አቅም መፍጠር አለባት።

''በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ተጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤትን አቋርጦ ተመልሶ አፍሪካ ህብረት የደረሰው የሶስትዮሽ ድርድር ዛሬም እልባት አላገኘም'' ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በግድቡ ሙሌት ሳትዘናጋ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳትና የግብጽን እንቅስቃሴ በንቃት መከታተል እንዳለባት አስገንዝበዋል።

የውሃ ሳይንስ ተመራማሪዋ መቅደላዊት መሳይ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የገጠማት ቅራኔ በሌሎች በዓባይ ላይ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች መደገም እንደሌለበት ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ከግድቡ ግንባታ ባለፈ የዓባይ ወንዝ ፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን ከኢትዮጵያ በኩል እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

ግብፅ የተፋሰሱ አገሮች ሊፈርሙት ያወጡትን "የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት" ባለመቀበል ከስምምነት መድረኩ እንደወጣች ተመራማሪዋ አስታውሰዋል።

''ከግድቡ ግንባታ ባለፈ በዓባይ ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በፍትሃዊነት መጠቀም የሚያስችል ድርድር ማድረግ ይጠበቃል'' ብለዋል።

የህዳሴ ግድቡ በኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬት ላይ የሚገነባ ሆኖ ሳለ ከግብጽ የሚሰማው የተቃውሞ ድምፅ ጠንካራ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር አደም አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ያላት አቋም አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በአገር ውስጥ ሰላምና አንድነት መፍጠር እንዲሁም ዘመናዊ ዲፕሎማሲ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብጽ በዓባይ ላይ የሚሰሩ የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን ለማስቀረት የሚፈጠሩ የውስጥ ችግሮችን ከማባባስ እንደማትመለስ ያለፉት 70 ዓመታት ስራዎቿ ምስክር መሆናቸውን ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም