ለመረሃ ግብሩ መሳካት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የፓርቲው ጽህፈት ቤት አመራሮች ገለጹ

42

ዲላ ሐምሌ 27/2012( ኢዜአ )ችግኝ በመትከልና በመከባክብ ለአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር መሳካት ግንባር ቀደም ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አመራሮች ገለጹ።

የጽህፈት ቤቱ አመራርና ሰራተኞች የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር በጌዴኦ ዞን  ዲላ ከተማ አኳሂደዋል።

በዚህ ወቅት የክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የሴክተሮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደግፌ መለስ የጌዴኦን ዞን ጨምሮ በክልሉ 4 ዞኖች በመዘዋወር ከ20 ሺህ በላይ ችግኝ መትከላቸውን ተናግረዋል።

ጽህፈት ቤቱ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር በስኬት እንዲጠናቀቅ ከማስተባበር ባለፈ በተግባር ንቁ ተሳትፎ በማድረግ  ለሌሎች አርአያ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተተከለውን ችግኝ በመትከልና በመከባክብ ለአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር መሳካት ግንባር ቀደም ኃላፊነታቸውን የመወጣቱን ስራም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ለምለም ሀምሳሉ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ የሊጉ አባላትን በማስተባበር ከ3 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል አቅደው  ወደ ትግበራ መገባቱን ተናግረዋል።

እስካሁንም ከ2  ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጓዳኝ በብልጽግና ፓርት ጽህፈት ቤት ስር የተለያዩ ዝርያ ያለው ችግኝ  በመትከልና ተከባክቦ በማሳደግ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን አስረድተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር የብልጽግናው ጉዞ መሰረት በመሆኑ ለስኬታማነቱ ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በጽህፈት ቤቱ የዴሞክራሲ ተቋማትና የሲቪክ ማህበራት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኝ ከፍያለው ናቸው።

የተተከለው ችግኝ እንዲጸድቅ በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች የቅርብ ክትትልና እንክብካቤ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ የሚያከናውነውን የችግኝ ተከላ ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

የጌዴኦ ዞን የፓርቲው የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ መኮንን ጪጩ  የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ በዞን ደረጀ በተለያዩ ተቋማት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ለየት ባለ መልኩ በዞኑ የችግኝ ተከላ ማከናወኑን አበረታችና ለሌሎችም ተነሳሽነትን የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ በችግኝ ተከላው መረሃ ግብር የሚያደርገውን የነቃ ተሳትፎ በእንክብካቤው ላይም እንዲደግመው  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም