''የውሃ ሙሌቱ ለትናንት ቁጭታችን ምላሽ የሚሰጥ ለዛሬ ርብርባችን ወኔ የሚያስታጥቅ ነው''-ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

112

አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2020(ኢዜአ) "የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ለትናንት ቁጭታችን ምላሽ የሚሰጥ ለዛሬ ርብርባችን ወኔ የሚያስታጥቅ ነው።" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ኢትዮጵያውያን ህልውናችንና ራዕያችን እውን የሚሆነው የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት በመከናወኑ ሳይሆን ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በፍትሃዊነት የምትገነባውን ግድብ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስተዋወቅን ታላሚ ያደረገ መርሀ ግብር "ድምፃችን ለግድባችን!" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ጎረቤት አገሮችን ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ ታላቅ ፕሮጀክት ነው።

ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ቁጭታቸው ምላሽ ያገኘበት ወደፊትም ከተባበሩ ሌሎች ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚችሉ ወኔ የሰነቁበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ አገሮች ጋር እንዲኖራት የምትፈልገው ግንኙነት የተፈጥሮ ሃብቷን በፍትሃዊነት መጠቀም በሚያስችል መርህ ላይ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን የግድቡ የውሃ ሙሌት መጀመር መዘናጋት የለባቸውም የሚሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ህልውናችንና ራዕያችን እውን የሚሆነው ግድቡ ሲጠናቀቅ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ እውን የሚሆነው ደግሞ ልዩነታችንን ወደ ጎን አድርገን በጋራ መዝመት ስንችል ነው ብለዋል።

ለኢትዮጵያውያን ግድቡ ለጥያቄያችን መልስ የሚሰጥ፤ ለችግራችን መፍትሄ የሚገልጽ እንዲሁም ለትውልዱ አዲስ ብርሃን የሚፈነጥቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለፍትህ የቆሙ አካላት ሆኑ ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም