የመከባበር እሴቶቻችን ተጠብቀው እንዲቆዩ የስነ ምግባር ትምህርት ማስተማር ያስፈልጋል--የሃይማኖት አባቶች

80

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 26/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያውያን ተከባብሮና ተዋዶ የመኖር እሴቶችን በሥነ ምግባር ትምህርት ማጠናከር እንደሚገባ የእምነት ተቋማት አባቶች አሳሰቡ።

ወጣቶች የሃይማኖት አባቶች የሚያስተላልፏቸውን መልካም አስተምሮ መቀበል እንደሚገባቸውም መክረዋል።

በአገሪቱ የትምህርት ተቋማት ሥነ ምግባርን የሚያጠናከር ትምህርት መሰጠት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ወጣቱ ትውልድ በትምህርት ተቋማት ሲሰጥ የነበረው የግብረ ገብ ትምህርት መቀጠል እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያን የዘርና የሃይማኖት ልዩነቶች ሳይገድቧቸው፣አንዱ የአንዱን እምነትና አመለካከት አክብሮና ጠብቆ ያለ አንዳች ልዩነትና መገፋፋት ለብዙ ዘመናት መዝለቃቸውን የታሪክ ምሁራንም፤ የተለያዩ ድርሳናትም ይመሰክራሉ።

የመከባበር፣ የመረዳዳትና አንዱ ለአንዱ ኩራት ሆኖ የኖረው ጥንታዊ እሴቶችን በሚመለከት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሃይማኖት አባቶችን አነጋግሯል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊና የድሬዳዋና ጅቡቲ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ “ሰው የሚያስብ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን በየጊዜው ስለ ሕይወቱ፣ ከሌላውም ጋር አብሮ መኖር እንዴት እንዳለበት ቅዱሳት መፅሐፍት ያስተምሩናል።

''የቤተክርስቲያን ሊቃውንትም፣ የእምነት ተቋማት አባቶችም ያለ ማቋረጥ ያስተምራሉ” ሲሉም ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ አሁን አሁን አንዳንድ ሰዎች ከኢትዮጵያውያን የማይጠበቅና ክቡሩን የሰው ሕይወት የሚቀጥፍና ንብረቱን የሚያወድም ተግባር እየተለመደ መምጣቱን ይናገራሉ።ኢትዮጵያውያን በዚህ ተግባር አንታወቅም በማለትም ጭምር።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በዑለማው የመስጅዶችና የአውቃፍ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሐመድ ሐሚዲን በበኩላቸው፤ ሠላምን ማስፈንና ሠላምን ማስተማር የምዕመናንና የእምነት አባቶች ኃላፊነት ነው ይላሉ።

የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ ወጣቶች ከስሜታዊነት ወጥተው ራሳቸውን እንዲገዙ መምከር እንዳለባቸውም ያስገነዝባሉ።

“ሠላምን በሚያደፈርስ፣በሚጎዳ ወይም በሚያውክ ነገር ላይ የሚሠማሩ ሁሉ ኃጥያአተኞች ናቸው፤ፈጣሪ ዘንድ ያስጠይቃቸዋል፤ የሚለው የሰው ክቡር ሕይወትንና ንብረት ሊጠበቅና እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል'' የሚል ትምህርት በየእምነቱ  እንደሚሰጥ ይናገራሉ።

የእምነት አባቶች ለወጣቶቹም ከስሜታዊነት እንዲርቁ የእስልምና አስተምህሮቱን በመጥቀስ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርሰቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶ በአገሪቱ እየታየ ያለው ግፍና ጥፋት የመጣው በትምህርት ተቋማቱ ሲሰጥ የነበረው የግብረ ገብና የሥነ ምግባር ትምህርቶች መሰጠት በማቆማቸው ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያውያንን ለማጋጨት ብዙ ተሠርቷል የሚሉት ፓስተር ፃድቁ፤ በዘርና በሃይማኖት ሕዝቡን ማጋጨቱ ትርፍ የማይገኝበት ኪሳራና ማንም አሸናፊ ከማይሆንበት እልቂት ውጭ የሚያመጣው ነገር እንደማይኖር ተናግረዋል።

በመሆኑም አሸናፊና ተሸናፊ የሌለባቸውን ዕልቂቶችና ግጭቶች እንዲቆሙ፣መከባበር እንዲሰፍንና የቀደሙት እሴቶቻችን እንዲጠበቁና ለቀጣዩም ትውልድ እንዲተላለፉ የሥነ ምግባር ትምህርት ዳግም መስጠት ስንጀምር ነው በማለት ይመክራሉ የሃይማኖት አባቶቹ።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ሲከሰቱ እየተስተዋለ ነው። በቅርቡ የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በተከሰተ ግጭት ከ167 በላይ ዜጎች ህይወት ሲያልፍ፤በሚሊዮኖች ብር የሚገመት ንብረት መውደሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም