በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ሁከት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ለፍርድ ቀረቡ

54
አሶሳ ሐምሌ 4/2010 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳና ሸርቆሌ ወረዳዎች ከሰኔ 16/2010 ጀምሮ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር የተጠረጠሩ አርባ ስድስት የክልሉ ፀጥታ መዋቅር አባላትና ግለሰቦች በትላንትናው እለት በአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረቡ። ፍርድ ቤቱ ነዋሪዎችን በብሔር በመከፋፈልና ወጣቶችን በማደራጀት በሰው መግደልና የመገድል ሙከራ፣ በአካልና በንብረት በደረሰ ጉዳት በተጠረጠሩት በነኮማንደር ኡስማን አህመድ የክስ መዝገብ የቀረቡ የአምስት ግለሰቦችን ጉዳይ ተመልክቷል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ቡድንም የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ ለማደራጀት የአስራ አራት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ በአስር ቀናት ውስጥ ተጠናቆ ለሐምሌ 12/2010 እንዲቀርብ አዟል። በሌላ በኩል በአሶሳ ዞን ሸርቆሌ ወረዳ ሰኔ 20/2010 በተፈጠረው የፀጥታ ችግር በመሳተፍ በሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የተጠረጠሩ አርባ አንድ ግለሰቦችም በአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ግለሰቦቹ ድምጽ አልባ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ፣ በቡድን በመንቀሳቀስ፣ የዜጎችን ተዘዋውሮ  የመኖርና የመስራት ህገ-መንግስታዊ መብትን በመጋፋት የተጠረጠሩ መሆናቸውንም መርማሪ ቡድኑ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ምድብ የወንጀል ችሎት ገልጿል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ አስደግፎ ለማቅረብ የጠየቀው የአስራ አራት ቀናት የጊዜ ቀጠሮም ተቀባይነት በማግኘቱ ለሐምሌ 18/2010 ተቀጥሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሰኔ 26 ቀን 2010 በዋለው ችሎት በአሶሳ ወረዳ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ አርባ ዘጠኝ የክልሉ ፖሊስ አባላትና ግለሰቦችን ጉዳይ ለመመልከት ለሃምሌ አስር ቀን 2010 ቀነ ቀጠሮ መስጠቱም ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም