በምሥራቅ ወለጋ እና ነቀምቴ ኮሮናን በመከላከሉ በኩል የሚስተዋለው መዘናጋት ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ነው

45

ነቀምቴ፣  ሐምሌ 26/2012 (ኢዜአ)  በምሥራቅ ወለጋ ዞንና ነቀምቴ ከተማ የኮሮና ቫይረስ በመከላከሉ በኩል የሚስተዋለው መዘናጋትና ቸልተኝነት ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል  አቶ ደሣለኝ ኩመራ እንደተናገሩት  በተፈጠረው መዘናጋትና ቸልተኝነት በአንዳንድ ወረዳዎች በሽታው በመከሰቱ እርምጃ እየተወሰደ ነው።

በሽታው የተከሰተባቸው ጊዳ አያና፣ በሊሙ እና በሐሮ ሊሙ ወረዳዎች ውስጥ እንደሆነ ጠቁመው፤ በእነዚህ ጨምሮ በአምስት ወረዳዎች በሽታውን ለመከላከል የትራንስፖርትና የገበያ አገልግሎት ለጊዜው እንዲቋረጥ መደረጉን አስታውቀዋል።

በሽታው በታየባቸው ወረዳዎች በተደረገው የናሙና ምርመራ በጊዳ አያና 34፣ በሊሙ ስምንት  እና በሐሮ ሊሙ የተወሰደው የናሙና ምርመራ ባይጠናቀቅም ለጊዜው አንድ ሰው በበሽታው መያዛቸው እንደተረጋገጠ ጠቅሰዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች ቡድን በየወረዳዎቹ በመዘዋወር ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውንም አቶ ደሣለኝ አስረድተዋል።

የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢና  የዞኑ  ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሥመራ ኢጃራ በበኩላቸው በዞኑ የተፈጠረውን መዘናጋት ተከትሎ የበሽታው ስርጭት በመታየቱም ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገር ደረጃ በሽታውን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎችን ለማስተግበርና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

በነቀምቴ ከተማ የተፈጠረው መዘናጋትና ቸልተኝነት አሳሳቢ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኘው አመራር ከግብረ ኃይሉ ጋር በመተባበር ለህብረተሰቡ ሁለተኛው ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ በርሶ ተመስጌን ናቸው።

የከተማው አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ተፈሪ ታደሰ የተፈጠረውን ክፍተት ለማስተካከል የፀጥታ ኃይሉ እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በሊሙ ወረዳ የገሊላ ከተማ ነዋሪ አቶ ገመቹ ቶለሣ በሰጡት አስተያየት በሽታውን በመከላከሉ በኩል በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው ቸልተኝነት አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው  በሽታው በመከሰቱ  ጥንቃቄ እንዲደረግ  በጤና ባለሙያዎች እየተነገረ ቢሆንም አሁንም የእጅ መታጠብ ፣ አካላዊ መራራቅን፣ የአፍና አፍንጫ ጭንብል አጠቃቀም ላይ መዘናጋት መኖሩን መታዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አዱኛ ገቾሌ በበኩላቸው በአካባቢያቸው በሽታው በመከሰቱ የትራንስፖርትና የገበያ አገልግሎት መቋረጡን ጠቅሰው፤ ቸልተኝነቱ አሁንም አሳሳቢ በመሆኑ ይህንን ለማስቀረት ሁሉም ትኩረት እንዲሰጠው ጠቁመዋል።

የነቀምቴ ከተማ ቀበሌ ዘጠኝ ነዋሪ አቶ ዶክተር ሞሲሳ  ኮሮናን ለመከላከል የተቀመጡ ሕጎች በአግባቡ በሥራ ላይ ባለመዋላቸው የበሽታው ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በከተማው ገበያ ፣ የትራንስፖርትና ሌሎች የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች  ያለው መዘናጋት ለማስቀረት  ከተማ አስተዳደሩ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም