ለጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት የወረዳ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ በትኩረት እንደሚሰራ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ

225

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 26/2012 ( ኢዜአ) የዜጎችን የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት እውን ለማድረግ የወረዳ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳን በአግባቡ መተግበር እንዳለበት የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በጥዬ ወረዳ የሚገኙ የቢላሎ ጤና ጣቢያንና የቡርቃ ጭላሎ ጤና ኬላን ጎብኝተዋል። 

በጉብኝታቸው ወቅት እንደተናገሩት የዜጎችን የጤና አገልግሎት ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የወረዳ ትራንስፎርሜሽን አገልግሎትና የጤና ኤክስቴንሽን ስራዎችን ማሻሻል ወሳኝ ነው። 

ወረዳዎችን ለተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ በማስቻል ጠንካራና የማይበገር የጤና ስርዓት እውን ማድርግ ይገባልም ነው ያሉት። 

የጤና አጀንዳዎችን ለማስተግበር የወረዳ አመራሮች፣ ህብረተሰቡና የጤናው ባለሙያዎች የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በአገሪቱ በሚገኙ ስምንት የወረዳ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ትራንስፎርሜሽንን በማረጋገጥ ለሌሎች ሞዴል እንዲሆኑ የተጀመረው ስራም ተስፋ ሰጭ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው የጎበኟቸው የጤና ተቋማት ቀደም ሲል አፈጻጸማቸው ከ50 በመቶ በታች የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ከ70 በመቶ ደርሷል።

በተለይ በእናቶችና ህጻናት አገልግሎት፣ በዳታ አያያዝ፣ በቤት ለቤት አገልግሎትና በአምቡላንስ አገልግሎት ወጤታማ መሆን ችለዋል።

በጤና መድህን ሽፋን አገልግሎት ግን ውጤታቸው አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ለቀጣይ መሻሻላቸው በአካባቢው ያሉ አመራሮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በሌሎች ክልሎች በሚገኙ የወረዳ ጤና ተቋማትም በቀጣይ ጉብኝት እንደሚደረግ ዶክተር ደረጄ ተናግረዋል። 

የቡርቃ ጭላሎ ጤና ተቋም ባለሙያ ሲስተር አለምጸሃይ ረጋሳ እንዳሉት ባልተመቻቸ የመሰረተ ልማት የአካባቢውን ህብረተሰብ የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ጥረት ተደርጓል።

በተለይ የመንገድ፣ የመብራት፡ የውሃና የኔትወርክ ችግር የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሙሉ አቅማቸው እንዳይከውኑ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል።

የጥዬ ወረዳ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ቡኒ ፈይሳ በበኩላቸው በወረዳው ለሚገኙ 121 ሺህ ሰዎች ጥራት ያለው አገልግሎት ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

የቢላሎ ጤና ጣቢያ ባለፉት ጊዚያት ከወረዳው ዝቅተኛ አፈጻጸም የነበረው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ70 በመቶ በላይ አፈጻጸም ማስመዝገብ ችሏል ብለዋል።

በተለይ የእናቶችና ህጻናትን ሞት በመቀነስ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን እውን በማድረግና የወረዳውን ነዋሪዎች ዳታ በማሳበሰብ ውጤታማ ሆኗል ብለዋል። 

የጤና መድህን ሽፋንን በማረጋገጥ በኩል ግን ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም የጸጥታ ችግርና በዚህ ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ የሚደርሰው መፈናቀል መሆኑን ገልጸዋል።

የወረዳ ትራንስፎርሜሽን ዓላማ ሞዴል ቀበሌዎችን ማፍራት፣ መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ወደ ከፍተኛ አፈጻጸም ማሸጋገርና ዜጎች በገንዘብ እጦት ለከፋ የጤና እክል እንዳይዳረጉ የጤና መድህን ሽፋንን ማረጋገጥ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም