የሚኒስቴሩ አመራሮችና ሠራተኞች 5 ሺህ ችግኞችን ተከሉ

72

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 26/2012 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው በአንድ ጀምበር 2 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ መርሃ ግብር የውሃ፤ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች ዛሬ 5 ሺህ ችግኞችን ተከሉ።

ኃላፊዎቹና ሠራተኞቹ በእንጦጦ ተራራ አካባቢ ችግኞቹን ተክለዋል።

የውሃ፤ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አብርሃ አዱኛ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ሚኒስቴሩ በአገር አቀፍ ደረጃ  እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ ለሦስተኛ ጊዜ ችግኞችን ተክለዋል።

ችግኝ በመትከልና የደን ልማትን በማስፋት ተጠቃሚ ከሚሆኑ ዘርፎች መካከል ሚኒስቴሩ የሚመራው ዘርፍ ዋነኛው መሆኑንም አስታውቀዋል።

በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአፈር መሸርሸርን ለማስቀረት ብቸኛው አማራጭ ችግኝ መትከልና ደን ማልማት እንደሆነ ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምም ቢሆን ተፈጥሯዊ የአጠባበቅ ዘዴ መከተል ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በከተማዋ እየተከናወነ ያለውን መርሃ ግብርን በመደገፍ በተከላው መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

ከደን ልማት የሚገኘው ጥቅምን በመገንዘብ ችግኝ የመትከል ተግባር የዘመቻ ሥራ ሊሆን እንደማይገባም ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።

ዜጎች በየአካባቢያቸው በአነስተኛ ቦታ ችግኝ መትከልን  ባህላቸው እንዲያደርጉ አቶ አብርሃ  ጠይቀዋል።

ሚኒስቴሩ ችግኞች በመንከባከብና በማጽደቅ ረገድም ከአካባቢው ማህበረሰብ ተቀናጅቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።  

የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ  ሠራተኞች እስካሁን 35 ሺህ 500 ችግኞች ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም