ኅብረተሰቡ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላላቸው ዓይነስውራን የድጋፍ እጁን አንዲዘረጋ ጥሪ ቀረበ

54

አዲስ አበባ  ሀምሌ 25/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ኅብረተሰቡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዓይነስውራን የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ ጠየቀ።

ማኅበሩ የኮሮና ቫይረስ መከሰት በተለይ በጎዳናና በዕምነት ተቋማቱ የሰው እጅ ጠብቀው ይተዳደሩ የነበሩ ሰዎች አሁን ላይ በችግር ውስጥ እንዳሉ ገልጿል።

በተጨማሪም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለሚገኙ ዓይነ ስውራን ድጋፍ እያደረግሁኝ ቢሆንም የምሰጠው ድጋፍ በቂ አይደለምና ኀብረተሰቡ ሊደግፈን ይገባል ብሏል።

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ኢስሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካታ ዓይነስውራን በየዕምነት ተቋማትና በየጎዳናው የሰው እጅ ጠብቀው ኑሯቸውን ይገፋሉ።

ታዲያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ የጎዳና እንቅስቃሴ በመገታቱና የእምነት ተቋማትም በመዘጋታቸው እነዚህ ዜጎች የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ተቸግረዋል ነው ያሉት።

ችግር ያለባቸውን ዓይነስውራን ለመለየት ምዝገባ በማካሄድ፣ የኑሮ ሁኔታቸውንና የችግራቸውን መጠን የሚገልፅ መጠይቅ እንዲሞሉ በማድረግ በመጀመሪያ ዙር 709 ችግረኞች መለየታቸውንም ገልጸዋል።

ሌሎችም በተለያየ ጊዜያት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ማኅበሩ ከውጭ ድርጅቶች ባገኘው ድጋፍ የምግብና የቤት ኪራይ ድጎማ እንዲሁም ምገባ የሚያደርግላቸው ዓይነስውራን መኖራቸውንም ነው አቶ ሱልጣን የገለፁት።

ድጋፉ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በደብረብርሃንና በደሴ ከተሞችም እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ማኅበሩ ያሰባሰበው ገንዘብ መኖሩንና ይህንንም ድጋፍ ባልደረሰባቸው ክልሎች ለሚገኙ ዓይነስውራን ለማዳረስ መታቀዱንም ተናግረዋል።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙት ዓይነስውራን ተሯሩጠው የሚያድሩና ቋሚ አድራሻ የሌላቸው በመሆናቸው የነዋሪነት መታወቂያ እንዳላገኙ ገልጸው በዚህ ሳቢያም በመንግስት መዋቅር የሚደረገው ድጋፍ እየደረሳቸው አለመሆኑንም ጠቁመዋል።

መንግስት ለእነዚህ የኀብረተሰብ ክፍሎች ለመድረስ ልዩ ሁኔታ ሊዘረጋ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ማኅበሩ የሚያደርገው ድጋፍ ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ ባለመሆኑ ኀብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

በማኅበሩ በኩል ድጋፍ ሲደረግ መስፈርት ተዘጋጅቶ ተደራራቢ ችግር ላለባቸው ቅድሚያ እንደሚሰጥም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር በ1953 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ዓላማውም የዓይነስውራን ዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ነው።

ከ12 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ማኅበሩ በአምስት ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች 32 ቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉት።

ይህ ማኅበር ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በአማካይ 200 ዓይነስውራን የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉንም መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም